ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተሰራው የወባ ወረርሽኝ ቁጥጥር ስራ ውጤታማ መሆኑ ተገለፀ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የድንገተኛ ኦፕሬሽን ማዕከል (EOC) ሳምንታዊ አፈጻጸም ግምገማ በበይነ መረብ አካሄዷል።

ለውይይት መነሻ የሚሆን የሳምንታዊ ሪፖርት በአቶ ዘርሁን መንገሻ አማካይነት የቀረበ ሲሆን በቀረበው ሪፖርት እንደተገለጸው የወባ በሽታ ወረርሽኝ በሕብረተሰቡ ጤና ላይ ስጋት ፈጥሮ የቆየ ቢሆንም በተደረገው ጠንካራ ቅንጅታዊ የመከላከል እና ህክምና ስራ የበሽታው ጫና በየሳምንቱ በአማካይ በ11% ቅናሽ እንዲሁም ተኝቶ ታካሚዎች በ19% ቅናሽ አሳይቷል ።

የደ/ም/ኢ/ህ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ውይይቱን በበይነ መረብ በመሩበት ወቅት የወባ በሽታ ወረርሽኝ ጫና እየቀነሰ መምጣቱ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተሰሩ የማፋሰስ፣ የማዳፈን ፣ የህ/ሰቡ አጎበር አጠቃቀም እየተሻሻለ መምጣቱ እና በጤና ኬላ ደረጃ ግብዓት በማቅረብ የምርመራና ህክምና ስራ በጠንካራ ክትትል በመሰራቱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከመስከረም እስከ ህዳር ባሉት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ የወባ ትንኝ የሚራባበት ወቅት በመሆኑ አሁን ላይ መሻሻል ባሳየው የወባ ስርጭት ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ ለትንኝ መራቢያ አመቺ የሆኑ ያቆሩ ቦታዎችን በህብረተሰብ ተሳትፎ የማፋሰስ እና የማዳፈን ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቶ ኢብራሂም አሳስበዋል።

ኃላፊው በአፅንዖት የገለጹት ጉዳይ ጥራታቸው እና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ ህገ- ወጥ የመድኃኒት ዝውውር እየተበራከተ በመምጣቱ መንግስት እየወሰደ ያለውን ጠንካራ ርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰባችን ህገወጥነትን ከመከላከል አንፃር ከመንግስት ጎን በመሆን ጥቆማ በመስጠት እገዛ እንዲያደርግ ገልጸው ለስራው ስኬት የሚዲያ አካላት ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ለወባ በሽታ ህክምና አገልግሎት የሚውል የመድኃኒት አቅርቦት እስከ ጤና ኬላዎች ድረስ እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ሀላፊው በመንግስት ጤና ተቋማት የሚሰራጩ መድኃኒቶች ለታለመለት ዓለማ ከማዋል አንጻር ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ጽዱ ኢትዮጵያ እንሽየቲቭ በክልላችን በንቅናቄ የተጀመረ ቢሆንም በቀጣይነት ተጠናክሮ መፈፀም እንዳለበት ገልፀው ከሐምሌ 1/2016 ዓ/ም ጀምሮ ሰው ተኮር አገልግሎትን በማጠናከር፣ ጽዱ የጤና ተቋማትን የመፍጠር እና የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአቅመ ደካማ ለሆኑ ሰዎች የነፃ ምርመራና ህክምና አገልግሎት በሁሉም የክልላችን ሆስፒታሎች ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የህጻናት ክትባትን ማጠናከር፣ የነፍሰ ጡር እናቶች ቅድመ ወሊድ ክትትልና የምግብ ምጣኔ ችግር ያለባቸውን ህፃናት እና ነፍሰ ጡር እናቶች ልየታ ተግባርም ቤት ለቤት ተከታትሎ የመስራት ስራ በትኩረት መሰራት እንዳለበትና በየደረጃ የሚገኙ የጤና አመራር በተገቢው እንዲመራ አቶ ኢብራሂም አሳስበዋል።
በጤና ሴክተር የተሰሩ ስራዎች መረጃ ጥራታቸው እና ወቅታዊነታቸውን ጠብቀው ወደ መረጃ ቋት የማስገባት አሰራር ሊጠናከር ይገባል ያሉት ሀላፊው ጥራት ያለው እና ወቅታዊ መረጃዎችን በመልሶ ማረጋገጥ መረጃ አያያዝ፣ሪፖርት አደራረግና መረጃን ለውሳኔ መጠቀም ልምድ እየዳበረ መሄድ እንዳለበት ገልጸዋል።

በክልላችን በሁሉም ዞኖች የመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ተለይተው እንዳሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ያስጠነቀቀ በመሆኑ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በተለይም በመጠለያ የሚገኙ ወገኖቻችን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እስከ ጤና ኬላ የሚገኙ መዋቅሮቻችን በመቀናጀት የተጀመረው ድጋፍ እና እንክብካቤ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል መደረግ አለበት ብለዋል።
በበይነ መረብ ውይይት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ጨምሮ ሁሉም አመራሮች እና ማኔጅመንት አባላት፣ የዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎች እና የዞንና የክልል ባለሙያዎች እንዲሁም የሆስፒታል ስራ አስኪያጆች ተሳትፈዋል።