ህብረተሰቡ በጤና ልማት ስራዎች ላይ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ እንደሆነ ተገለጸ።

በካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ መሻ ቀበሌ በህብረተሰብ ተሳትፎ የተገነባው ጤና ኬላ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በምረቃ ፕሮግራሙ የመሻ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ተረፈ ማሮ ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ የጤና ተግባር የእኔ ነው በማለት ህብረተሰቡ ያለማንም አስገዳጅነት በእራሱ ፍላጎት ሀብት በማዋጣት ዛሬ ላይ የሚመረቀውን ጤና ኬላ እና የጤና ኤክስቴንሽን መኖሪያ ቤት ከማስገንባት ባለፈ ቀበሌው በጤና ሞዴል ሆኖ እንዲመረቅ የድርሻውን ተወጥቷል ሲሉ ገልጸዋል።
ለጤና ኬላ እና ለጤና ኤክስቴንሽን መኖሪያ ቤት ግንባታ በካሽ፣ በቁሳቁስና በጉልበት 1 ሚሊየን 6 መቶ 78 ሺህ 5 መቶ ብር ከህብረተሰቡ በማስተባበር ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት እንደሆነም አቶ ተረፌ አብራርተዋል።
ቀበሌው ከዚህን በፊት በጤና ዘርፍ ቀዳሚ እንደነበር የገለፁት የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ተክሌ አሁን ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት የሚመሰገን ነው ብለዋል።
በወረዳው የጤና ፓኬጆችን በሟሟላት 2ተኛ ቀበሌ ሆኖ መመረቁን የጠቆሙት ኃላፊው ተግባሩ እንዲሳካ በየደረጃው ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጠሎ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትርሴ ሸታቸው ህብረተሰቡ በጤና ልማት ስራዎች ላይ እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት እና ህዝብ ተቀናጅቶ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለትካዊ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚችል የመሻ ቀበሌ ማህበረሰብ በተግባር አሳይተውናል ያሉት አስተዳዳሪው ጤና ኬላው በአቅራቢያው ከሚገኘው ጤና ጣቢያ እና ሆስፒታል ጋር በመተሳሰር የህብረተሰቡን ጤና እንዲያስጠብቅ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ህብረተሰቡ ለጤናው ዘርፍ ላደረገው ሁሉ አቀፍ ትብብር ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ አትርሴ በትምህርት፣ በግብርና እና በሌሎችም ግንባር ቀደም መሆን እንዳለባቸው ጥሪ አስተላልፈዋል።
ለዘርፉ ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የዕውቅና ሰርትፊኬት ተበርክቶላቸው ፕሮግራሙ ተጠናቋል።
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የወረዳ አስተባባሪዎች፣ አመራሮች፣ የዞን ደጋፊ ባለሙያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎች ባለድርሻ ተገኝተዋል።
ዘገባው የጠሎ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።