የሆስፒታሉን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ።

በኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በአቶ ታከለ ተሰፉ የተመራው ልዑክ የአመያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ጉብኝት አድርገዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪና የሆስፒታሉ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታከለ ተስፉ የሆስፒታሉ አገ/ሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንዲመጣ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን አመላክተው በባለፈው ቦርድ ውይይት ወቅት የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ከመፈፀም አንፃር የተጀመሩ ስራዎች በበለጠ ተጠናክረው እንዲመሩ አስገንዝበዋል።
ሆስፒታሉን ወደጠቅላላ ሆስፒታል ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር የአገ/ሎት መስጫ ማዕከላት ግንባታዎችን ማስፋፋትና የግብዓት አቅርቦት ደረጃ በደረጃ እየተከናወኑ እንደሚሄዱ አንስተው የውስጥ አገ/ሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በሙሉ አቅም መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአመያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ አሻ ሆስፒታሉ የጽዱ ኢትዮጵያ ጽዱ ሆስፒታል ኢንሺየቲቭ ውስጥ ከተመረጡ 9 ሆስፒታሎች መካከል ክልሉን ወክሎ የተመረጠ ብቸኛ ሆስፒታል ሆኖ እየሰራ መሆኑን ገልፀው ከተጣለበት ተግባር አንፃር የህብረተሰቡን እርካታ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል ።
ሆስፒታሉ የእናቶችንና ህፃናትን ጤና አገ/ሎት በማሻሻል፣ ስርዐተ ምግብ አገ/ሎት በማሳደግ፣ የተቀላጠፈ የህክምና አገ/ሎት በመስጠት፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር በተለይም ወቅታዊ የወባ በሽታ በመከላከል በትኩረት መስራቱን አስረድተዋል።
ሆስፒታሉ በዞኑ ብቸኛ ሆስፒታል በመሆኑ የአጠቃላይ ሆስፒታል አይነት አገ/ሎት እየሰጠ ነው ያሉት አቶ አለማየሁ የሚስተዋለውን የመድኃኒት እጥረት ለመቅረፍ በመንግስት ለማስጀመር የታቀደውን የማህበረሰብ መድኃኒት ቤት መክፈትና የሰው ኃይል ማሟላት የበለጠ መተኮር እንደሚገባ አንስተዋል።
በቀረበው የ2016 በጀት ዓመት ሪፖርት ላይ ባለፈው ሩብ ዓመት በቦርድ ውይይት የተቀመጡ ዉሳኔዎችን ተፈፃሚ ከማድረግ አንፃር የሰው ኃይል ለማሟላት ባሉ 2 ስፔሻሊስቶች ላይ ተጨማሪ 2 ስፔሻሊስቶችን በመጨመር 4 ስፔሻሊስቶች ማድረጋቸው፣ ከሌሎች 2 ሆስፒታሎች ጋር ልምድ ልውውጥ በማድረግ የበጀት አስ/ር ማስተካከል፣ ለተኝቶ ታካሚዎች የምግብ አቅርቦት መጀመር፣ የውስጥ ግብዓት ማሟላትና መሠል ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ተገልጿል።
በዞኑ በከፍተኛ ሁኔታ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ሆኖ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ በመከላከል ለ1,200 ለሚሆኑ አባወራዎች ቤት ለቤት ትምህርትና ክትትል እንዲሁም ተመርምረው ወባ ለተገኘባቸው 734 ታካሚዎች የህክምና አገ/ሎት መስጠታቸውም ተነግሯል።
የጉብኝቱ ተሳታፊ የሆስፒታሉ ቦርድ አመራር አካላትና አባላት በሆስፒታሉ የሚከናወኑ ተግባራት የጽዱ ኢትዮጵያ ጽዱ ሆስፒታል ኢንሺየቲቭ መሠረት አድርገው እንዲከናወኑ ጠቁመው የተጀመረውን የጤና መድህን አገ/ሎት በበለጠ ማሳደግ፣ የመረጃ አደረጃጀት በበለጠ ማሻሻል፣ የኦዲት ስራዎችን በየወቅቱ ማከናወንና የእናቶች ማቆያ የበለጠ ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀው የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል የበጎ ፍቃድ አገ/ሎት እንዲስፋፋ ማድረግና የጤና ኤክስቴንሽን ስራን መደገፍ እንደሚያሻ ገልፀዋል።
የቦርዱ አባላት ዶ/ር ተመስገን ደግሰው የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር እንዲሆኑ ወስነዋል።
ዘገባው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።