መሠረታዊ የጤና ፓኬጆችን በመተግበር ቀበሌዋን የተሻለ ሞዴል ለማድረግ እንደሚሰሩ ተገለፀ፤

በምዕራብ ኦሞ ዞን በማጂ ወረዳ በመሠረታዊ የጤና ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግ የኩሽት ቀበሌን የተሻለ ሞዴል ለማድረግ እንደሚሰሩ ተገልጿል።
በዛሬው ዕለት በኩሽት ቀበሌ በተካሄደ ጉብኝት በወረዳው ከተመረጡ ቀበሌያት የተውጣጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን መሠረታዊ የጤና ፓኬጆችን ተግባራዊ ባደረጉ ሞዴል አርሶ አደሮች ቤት ጉብኝት ተካሂዷል።
ወ/ሮ ኦርኔ ወንበር የኩሽት ቀበሌ ነዋሪ ስትሆን በጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ትምህርት ተግባራዊ በማድረጓ ሞዴል ሆና መመረጧን ገልፃለች።
ወ/ሮ ኦርኔ አያይዛም እናቶች ሆስፒታል መውለድ እንዳለባቸውና ወላጆች ልጆቻቸው በመንከባከብ የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ለብቻቸው መፀዳጃ ቤት እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባቸዋል ብላለች።
ወጣት አበበ ጫድንባብ በተመሳሳይ የኩሽት ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን መሠረታዊ የጤና ፓኬጆችን ተግባራዊ ከማድረግ በተጨማሪ በከብት ማድለብ ሥራ ላይ መሰማራቱን ገልፆ በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ ገልጿል።
ሲ/ር ትዝታ ካሳ በማጂ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የጤና መኮንን እና የኩሽት ቀበሌ ሱፐርቫይዘር ስትሆን ቀበሌዋን ሞዴል ለማድረግ በተሰራ ስራ ውጤት ማምጣት እንደተቻለ ገልፃ በቀጣይ የጤና ፓኬጆችን በሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ሞዴል ቀበሌ ለመፍጠር በትኩረት እንሰራለን ብላለች።
የጌባርኩ ቀበሌ ጤና ኤክስቴንሽን ወ/ሮ ሠላማዊት ባንትይርጋ፦ በጉብኝቱ የተሻለ ተሞክሮ መቅሰሟን ጠቅሳ በተለይም መፀዳጃ ቤት፣ የሰው ልጅ እና እንስሳት ለየብቻ እንዲኖሩ መደረጉ የተሻለ ተሞክሮ መሆኑን ጥቅሳ በቀጣይ ያገኘችውን ልምድ ወደ ቀበሌዋ በመውሰድና ጽዱ መንደሮችን በመፍጠር ነጭ ሰንደቅ ዓላማ ለማውለብለብ በትኩረት እንሰራለን ብላለች።
የኩሽት ቀበሌ ጤና ኤክስቴንሽን ወ/ሮ ንፁህ ደሴ በበኩላቸው የኩሽት ቀበሌ ከዚህ በፊት ሞዴል እንደነበር ጠቅሳ ቅንጅታዊ ሥራና ድጋፋዊ ክትትሉን በማጠናከር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልፃለች።
የኩሽት ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቻሙ ያባክ በቀበሌው ደችት መንደርን ሞዴል ማድረግ የተቻለ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ በጤና፣ በግብርናውም ሆነ በትምህርቱ ዘርፍ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ሞዴል ቀበሌ ለመፍጠር እንደሚሰሩ ገልፀዋል ሲል የማጂ ወረዳ ኮሙኒኬሽን መዘገቡን ጠቅሶ የዘገበዉ የምዕራብ ኦሞ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።