መንግሥት የዜጎችን የምግብ ዋስትና እና ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሠራ ይገኛል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
የኢትዮጵያ የምግብ ስርዓት፣ ኒውትሪሽን እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድን የ2016 ዓ.ም አፈጻጸም ሪፖርትና የ2017 ዕቅድ ግምገማ የፌደራል እና የክልሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በድሬዳዋ ከተማ ተካሄዷል።
መድረኩን በይፋ የከፈቱት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጤናማ ትውልድን መገንባት የሀገር ግንባታ ምሰሶ በመሆኑ የህፃናት አካላዊና የአዕምሮ ጤና ግንባታ ሥራ የመንግስት ትልቁ አጀንዳ ነዉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የመቀንጨር ችግርን በ2022 ዓ.ም ዜሮ ለማድረግ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡበት ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ለመተግበር በክልሎች ተቋማዊ አደረጃጀት መፈጠሩ ትልቅ እርምጃ መሆኑንም አንስተው እስከ አሁን ያላደራጁ ክልሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ አደራጅተው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
አንድ ህፃን ከማህፀን ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ በተስተካከለ ስርዓተ ምግብ እንዲያድግ በማድረግ መቀንጨርን ማጥፋት የሚቻል መሆኑን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን አመራሩ በቁርጠኝነት ስራዉን ሊመራ ይገባል ብለዋል።
መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ሀገር በቀል የሆነውን የሰቆጣ ቃልኪዳን ለመተግበር አስፈላጊውን በጀት እየመደበ በመሆኑ ክልሎችም ለሀገርና ለትውልድ ጥቅም የሚሰራውን ንቅናቄ ውጤታማ ለማድረግ የአቻ በጀት ምደባን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
እንደ ሃገር በጤናው ዘርፍ ፍትሀዊ፣ ጥራት ያለውና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት በማስፋፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማህበረሰብ ጤና መድህን ስርዓት ከአንድ ሺህ በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች እየተተገበረ እንደሆነ አንስተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፣ ጤናማ፣ አምራች እና በሁሉም ዘርፍ ብቁ ዜጎችን ለማፍራት በኒውትሪሽንና በሰቆጣ ቃልክዳን እንዲሁም ጤና መድህንን ተደራሽ በማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት 39 በመቶ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ለመቀንጨርና 11 በመቶዎቹ
ለመቀጨጭ የተጋለጡ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የማህበረሰቡን የአመጋገብ ባህል ለማሳደግ፣ የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የህብረተሰቡን ባለቤትነት ያሳተፈ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ቅንጅትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳት ሚና የጎላ ነው ብለዋል።
ጤና ሚኒስቴር በየደረጃው ላሉ ተፈፃሚ አካላት የማይቋረጥ ክትትል እና ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ያነሱት ዶክተር መቅደስ በተያዘው የ2017 አመት ዕቅም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ የግብርና ምርትን በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት በማምረት ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ እንዲሁም ሌሎች በግብርናው እንደ ሃገር እየተከናወኑ የሚገኙ ጉዳዮች ከስርዓተ ምግብ ተኮር ግብርና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል።
በመድረኩ ላይ በስርዓተ ምግብ አስፈላጊነት፣ የሰቆጣ ቃልክዳን እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የ2016 አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2017 ዕቅድ የቀረበ ሲሆን በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱም በስርዓተ ምግብ ችግር ምክንያት የሚከሰተዉን መቀንጨርና መቀጨጭን ዜሮ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ስራውን በባለቤትነት ሊመሩ ይገባል ተብሏል።
በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራት እንዳለበት በውይይቱ የተነሳ ሲሆን ስራዎችን በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ ሁሉም ሚናውን መወጣት እንዳለበት አቅጣጫ ተሰጥቷል።
ዘገባው የጤና ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር ገጽ ነው።