ማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ጥራት ያለውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል የድጋፍና ክትትል ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።
በሸካ ዞን በማሻ ከተማ በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ለሆነዉ ለማሻ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ5 መቶ ሽህ ብር በላይ የሚገመት የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ ግብዓቶች ድጋፍ ማድረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ በህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ከበደ እንደገለጹት የማሻ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የግንባታ ስራ እና የቁሳቁስ ማሟላት ስራ ተጠናቆ በቅርቡ ወደ ስራ መግባቱ ለማሻና አካባቢው ህብረተሰብ ጤና አገልግሎት ላይ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የማሻ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የግንባታ ስራ በ2008 ዓ/ም በቀድሞ የደቡብ ብ/ብ/ህ/ክልል መንግስት የተጀመረ መሆኑን ያስታወሱት ዳይረክተሩ ግንባታው በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት የቆየ ኘሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል።,
ክልሉ የግንባታ ስራው ሂደት እንዲፋጠን በጀት በመመደበ እና ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የግንባታ ሂደት በጥራት እንዲሰራ ቁጥጥር እና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
ለሆስፒታሉ የስራ ማስጀመሪያ አገልግሎት የሚውል የህክምና መሳሪያዎች ኪት ከ”ህውማን ብሪጅ ኢትዮጵያ” (Human Bridge Ethiopia) ከተባለ ግብረ- ሰናይ ድርጅት በድጋፍ ማግኘታቸውን የገለጹት አቶ አበበ መሳሪያው ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ለማድረስ በውጭ አገር የሚገኙ የሸካ ዞን ዲያስፖራ አባላት ሙሉ የትራንስፖርት ወጭ መሸፈናቸውን ገልጸዋል።
ይህ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት በቀጣይም በክልላችን ግንባታዉ ተጠናቅቆ አገልግሎት ለሚጀምሩ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታሎች እና ሌሎች ሆስፒታሎች የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ተግባር የክልሉ ጤና ቢሮ የሂውማን ብሪጅ ኢትዮጵያን እና የተቋሙን አመራር ላቅ ያለ ምስጋና ያቀርባል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ለሆስፒታሉ ስራ ማስጀመሪያ የሚሆን ከ5 መቶ ሽህ ብር በላይ የሚገመት መድሀኒትና የህክምና መገልገያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዉ ሆስፒታሉ በቀጣይ ጥራት ያለውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ እንዲሰጥ ለማስቻል ድጋፍ እና ክትትል እንደሚደርግም ገልጸዋል።
በመጨረሻም የደቡብ ም/ኢ/ህ/ክ/መንግስት እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሆስፒታሉ ግንባታ ከተጀመረበት ተመርቆ ስራ እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ ስላደረጉት ድጋፍ በክልሉ ጤና ቢሮ ስም አመስግነዋል አቶ አበበ ከበደ።