በሆስፒታሎች ምቹ የሆነ የፋርማሲ አሰራር ስርዓትን በመዘርጋት ግልጸኝነት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ለኦዲት ምቹ የሆነ የፋርማሲ (Auditable pharmaceutical transaction service) አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስልጠና ከዳውሮ እና ከኮንታ ዞኖች ጠቅላላ እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ለተወጣጡ ባለሙያዎች በታርጫ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ የመድሀኒት እና የህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ከበደ በሆስፒታሎች ለኦዲት ምቹ የሆነ የፋርማሲ አሰራር ስርዓትን በመዘርጋት ግልጸኝነት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአሰራር ስርዓቱን ተግባራዊ ለማድረግ በደ/ም/ህ/ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁሉም የጠቅላላ እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ስራ አስኪያጆች፣ የፋርማሲ፣ የዕለት ገቢ ሰብሳቢ እና የውስጥ ኦዲተር ባለሙያዎች በአራት ዙር በቦንጋና በታርጫ ማዕከል ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል።
በአራት ዙር ከሚሰጠው ስልጠና አንደኛው ዙር በቦንጋ ማዕከል የተሰጠ ሲሆን ሁለተኛው በታርጫ ማዕከል ከዳውሮ እና ከኮንታ ዞኖች ውስጥ ከማገኙ አጠቃላይ እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ለተወጣጡ ስራ-አስኪያጆች እና ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል አቶ አበበ ከበደ ።
በሁለቱም ማዕከላት በአራት ዙር የሚሰጠው ስልጠና ሲጠናቀቅ ለኦዲት ምቹ የሆነ የፋርማሲ አሰራር ስርዓት በክልልሉ ውስጥ በሚገኙ በሁሉም ጠቅላላ እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ወጥ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
አሰራሩ በፊት በጤና ተቋማት የሚገኙ የፋርማሲ አገልገልግሎት ውስጥ የመዲሀኒት ስርጭት እና ገንዘብ አሰባሰብ ላይ ግልጸኝነት እንዲፈጠር ዕለታዊ የፋርማሲ አገልግሎት ኦዲት እንዲደረግ በማድረግ ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲሰፍን ያደርጋል ብለዋል።
የፋርማሲ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች ለተገልጋይ እና ለአገልግሎት ተቀባዩ ምቹ ከማድረግ አንጻር የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የስልጠና አስተባባሪ እና በክልሉ ጤና ቢሮ ህክምና አገልግሎቶች ዘርፍ የፋርማሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዓለምጸጋ አየለ APTS (Auditable pharmaceutical transaction service) ስልጠና ከዚህ በፊት ለኦዲት ምቹ ያልሆኑ የሪፖርት ጥራትና ወቅታዊነት ፣ የመድሀኒት ስርጭትና የተጠቃሚዎች ምጣኔ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህ የፋርማሲ አገልግሎት ስልጠና ግልጸኝነት እና ተጠያቂነት ለማምጣት ወሳኝ መሁኑን ገልጸው ሰልጣኞች በአሰራሩ በቂ ግንዛቤ ይዘው እንደሚመለሱ ለማስቻል በስልጠናው የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡም ገልጸዋል።
ከጥር 26 -28/2017 ዓ/ም ድረስ በታርጫ ከተማ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ስልጠና በኮንታ እና በዳውሮ ዞን ውስጥ ከሚገኙ የአጠቃላይ እና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ለተወጣጡ የፋርማሲ ፣ የዕለት ገቢ ሰብሳቢ እና ኦዲተር ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል አቶ አለምጸጋ።