በሚዛን ማረሚያ ተቋም ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች ለሁለት ቀናት የሚቆይ የበጎ ፈቃደኞች የህክምና አገልግሎት መሰጠት ጀመሩ፣

የህክምና አገልግሎቱን ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ፣ ከዩናቨርሲቲው ማስተማሪያ ሆስፒታል የተወጣጡ በጎ ፈቃደደኛ የህክምና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ግብአት ቁጥጥር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አሰፋ እንዳሉት የክልሉ ጤና ቢሮ ከታች ከሚገኙ የጤናው መዋቅርና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ከነሐሴ 1 እስከ 30 /2016 ዓ/ም ለ1 ወር በጤናው ዘርፍ ልዩ የበጎፈቃድ ተግባራትን እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ ስራው ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር፣ የጡት ካንሰር እና ለሌሎችም ህመም ዓይነቶች ምርመራና ህክምና አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድሙ አይሳ በበኩላቸው የደም ልገሳና ወባን የመከላከል ተግባራት የክረምት ወራት የበጎፈቃድ አካል ሆነው በትኩረት ይሰራባቸዋል ብለዋል።
ሃላፊው አክለውም በሚዛን ማረሚያ ተቋም ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች የተጀመረው የበጎ ፈቃድ ነጻ የምርመራና ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው ነጻ የህክምና አገልግሎት 2 ስፔሻሊስት ሃኪሞች፣ 5 ጠቅላላ ሃኪሞች፣ 3 ነርሶች፣ 2 የላብራቶሪ ባለሙያዎች፣ 2 የፋርማሲና በሌላ ሙያ ውስጥ ያሉ ደጋፊዎች የተካተቱበት የህክምና ቡድን መሆኑ ተነግሯል።
የነጻ ህክምና ቡድኑ አስተባባሪዎች በሰጡት አስተያየት ነጻ ህክምናው ጠቅላላ ህክምና፣ የጥርስ ነቀላና ፣ የወባ ምርመራና ህክምና አገልግሎት ለታራሚዎች የሚሰጡ ይሆናል።
የህክምና ቡድኑ ሙሉ የመድሃኒትና ሌሎች ግብአቶችን ከራስ፣ ከበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ በማሰባሰብ ከ80 ሺህ ብር በላይ ግብአት አሟልቶ ህክምና አገልግሎት ጀምረዋል።