በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ለጤና ባለሙያዎች፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችና ባለድርሻ አካላት የአንጀት ጥገኛ ትላትልና የቢልሃርዝያ በሽታ መከላከያ መድሃኒት አወሳሰድ ላይ ስልጠና ተሰጠ።
በመድረኩ የጤና የስራ ክህሎት ንግድ ኢንተርፕራይዝ ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ሃላፊና የከንቲባ ተወካይ አቶ ምትኩ ጢሞቲዮስ፣ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወንድሙ ዓይሳ፣ የትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ስንታየሁ ጋይድን ጨምሮ የዞን ጤና መምሪያ አስተባባሪዎች፣ የጤና ጽህፈት ቤት ባለሙያዎች፣ ርእሳነ መምህራን፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችና የትምህርት ቤቶች የጤና ክበብ ተጠሪ መምህራን ተገኝተዋል።
ትኩረት ከሚሹ የሀሩራማ በሽታዎች መካከል አንዱ የቢልሃርዝያ በሽታ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በሽታውን ለመከላከል ተከታታይነት ያላቸው ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በሽታውም የአንጀት እና የሽንት ቧንቧ ቢልሃርዝያ ወይም ተብለው በሚጠሩ በቀንድ አውጣ ውስጥ በሚኖሩ ተዋስያን አመካይነት የሚከሰት ሲሆን የሚተላለፍበት መንገድም አንድ ሰው የቀንድ አውጣ ጥገኛ ተህዋስ (የቢልሃርዝያ እጭ) በተፈለፈለበት ውሃ ውስጥ ሲገባ ወይም ሲታጠብ ሊያዝ ይችላል ተብሏል፡፡
በቀንድ አውጣው የተፈለፈለው ጥገኛ ተህዋስ (የቢላሃርዝያ እጭ) ቆዳን በመብሳት ወደ ሰውነት ውስጥ ዘልቆ በቀጥታ ወደ ሽንት ቱቦ ወይም ወደ አንጀት ውስጥ በመግባት እና በመራባት ጉዳት ያደርሳል፡፡
ይህ ዑደት የሚቀጥለው በበሽታው የተያዘ ሰው በወንዝ አካባቢ ሲሸናና ሲፀዳዳ የቢልሃዝያ እንቁላል ወደ ውሃው ስለሚገባ ነው፡፡ በሽታው ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር የሚያስከትል ሲሆን በበሽታው በከፍተኛ ደረጃ ተጠቂ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም እድሜያቸው ከ5-14 ለሆኑ ልጆች የፕራዘኳንታል መድሃኒት እደላ ይደረጋል ተብሏል፡፡
የመድሃኒት እደላ የሚሰጠውን የበሽታ መከላከያውን ኪኒን ከወሰዱ በኋላ በአስከፊው የቢልሃርዝያ በሽታ ዳግም እንዳይያዙ ለመከላከል ያለመ ነው።
በመድረኩ የ2017 ዓ/ም ሶስት ወራት በወባ መከላከል የተከናወኑ ተግባራትና በቀጣይ የሚከናወኑ የወባ ንቅናቄ ስራዎች ዙሪያ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ዘገባው የሚዛን አማን ከተማ አሰተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።