በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት በመታቀፋቸው ከከፍተኛ የህክምና ወጪ እየታደጋቸው መሆኑን በዳውሮ ዞን የከጪ ወረዳ ተገልጋዮች ገለፁ::
በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት በመታቀፋቸው ከከፍተኛ የህክምና ወጪ እየታደጋቸው መሆኑን በዳውሮ ዞን የከጪ ወረዳ ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች ገልጸዋል።
በ2017 አባልነት እደሳ ወቅት ከ4ሺህ 8 መቶ በላይ አዲስና ነባር አባላትን በዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት አስታውቋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን ለማግኘት በአመት አንድ ጊዜ በቆረጡት የአባልነት ክፍያ ካሉበት አካባቢ የጤና ተቋም ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎቶችን እያገኙ መሆናቸውን ከወረዳው ነዋሪዎች መካከል አቶ ከድር ወላንቾ እና ወ/ሮ ለምለም ዳዕሞ ተናግረዋል።
በገንዘብ አቅም ማነስ ምክንያት የአባልነት ክፍያውን መፈፀም ባለመቻላቸው በወረዳው መንግስት በኩል ክፍያ ተፈፅሞላቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር የህክምና አገልግሎት በጤና መድህን እያገኙ መሆናቸውን ወይዘሮ ፀዳል ኦሱ እና በካል በየነ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።
ህመም ሲከሰት በገንዘብ በመታከም ሊያስወጣቸው የሚችለውን ከፍተኛ ወጪ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆን እንዲታከሙ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል።
ሌላኛው ተጠቃሚ አቶ ተፈራ ሽፈራው በበኩላቸው፤ ዘንድሮ ድንገት በተከሰተባቸው የጤና ጉዳት ምክንያት ከከጪ ጤና ጣቢያ እስከ ታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል ድረስ ለተከታታይ ለ6ወራት በጤና መድህን አባልነት ህክምና በማግኘታቸው ከ38ሺህ በላይ ገንዘብ ሊያስወጣ የሚችለውን አገልግሎት በአባልነታቸው ብቻ ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።
በዘርፉ የተገልጋይ ማህበረሰብ እርካታን በሚያሳድጉ ተግባራት ላይ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም በወረዳው የከጪ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ኮቾ ጠቁመዋል።
የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብዙአየሁ ዘርሁን እንደገለጹት፤ በወረዳ ደረጃ ከ4ሺህ 8 መቶ በላይ ነባር እና አዳዲስ አባላትን በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ለማሳቀፍ የታቀደ ሲሆን ገንዘብ መክፈል ለማይችሉ አረጋውያንም የተለያዩ የእርዳታ ሁኔታዎችን በማመቻቸት እየተሠራ ነው።
በተለይም ድንገተኛ ህመም ሲከሰት አርሶ አደሮች ከብቶቻቸውንና ንብረቶቻቸውን ሽጠው ከመታከም የጤና መድህን አባል በመሆን አንድ ጊዜ በከፈሉት ብቻ ከጤና ጣቢያ እስከ ከፍተኛ የጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የማስገንዘብ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ የጤና መድህን አባል በመሆን ከፍተኛ ወጪ ሊያስወጣቸው የሚችለውን የህክምና አገልግሎት በዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አቶ ብዙአየሁ ዘሪሁን ጥሪ አቅርበዋል።
የወረዳው ማህበረሰብ በጤና መድህን አገልግሎት ታቅፎ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የማስገንዘብ ሥራ በተቀናጀ አኳኋን እየተፈፀመ እንደሚገኝ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ውለታው ሁሴን ገልፀዋል ሲል መዘገቡን ከዳውሮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።