በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተጀመሩ የወባ ወረርሸኝን የመግታት ዘመቻዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፌ-ጉባኤ በወይዘሮ ፀሀይ ዳርጫ የተመራው የድጋፍ ቡድን በዳውሮ ዞን አሁናዊ የወባ ወረርሽኝ ቁጥጥር ምላሽ ድጋፍ ክትትል ግኝት ግብረ መልስ ሪፖርት አቅርቧል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ፀሀይ ዳርጫ እንደገለፁት
የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል የተዘረጉ ቅንጅታዊ አሰራሮችና የአመራር ቁርጠኝነት አጠናክሮ በማስቀጠል ወረርሽኙን በዘላቂነት በመግታት የማኅበረሰቡን ጤና ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
የወባ ወረርሸኝ እየተፋፋመ መምጣቱን አሰመልክቶ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮና የክልሉ ምክር ቤት በመቀናጀት የድጋፍዊ ቁጥጥር ሥራ እየሰሩ መቆየታቸውን በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል ዳይሮክተሬት ዳይሮክተር ዶ/ር እንዳለ ሣይሌ ገልፀዋል።
የወባ ወረርሽኝ መከላከል ጉዳይ የሁሉም ተቋማት ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል ያሉት ዶ/ር እንዳሌ አሁን ላይ የወባ ቁጥጥር ዘመቻ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ወባን ማጥፍት ከእኔ ይጀምራል በሚል መርህ ሀሳብ በክልሉ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የማዳፈን፣ የማፋሰስ እንዲሁም የፅዳት ዘመቻ ሥራዎች ሲተገበሩ መቆየታቸው በርፖርቱ ተመላክቷል።
በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወናቸውና ከሀይማኖት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች በመሠራታቸው ወረርሽኙ እየቀነሰ መምጣቱን ከየወረዳው የቀረበ ርፖርት ያትታል።
የዳውሮ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አላንቦ የወባ ወረርሽኝ የሚያደርሰውን ጫናን ለመቀነስ የማኅበረሰብ ድርሻ የጎላ በመሆኑ በቀጣይም በሚደረጉ ማናቸውም ዘመቻዎች ላይ በመሳተፍ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠቁመዋል።
ተሳታፊዎቹ ከእስካሁኑ በተለየ መልኩ የመከላከሉንና የመቆጣጠሩን ተግባር ለመተግበር የጋራ መግባባት ላይ የደረሱ ሲሆን ለሚስተዋሉ ማነቆች ከክልሉ ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳሰበዋል።
ዘገባው የዳውሮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።