በምዕራብ ኦሞ ዞን ከ47 ሺህ በላይ ህጻናት የፖሊዮ ክትባት ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
በምዕራብ ኦሞ ዞን የፖሊዮ ክትባት አሰጣጥ አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት የስልጠና መድረክ ተደርጓል።
በመድረኩ የዞኑ ጤና መምሪያ ሃላፊ ተወካይ አቶ አባይነህ ጱሌጂ በዞኑ ከየካቲት 14 ጀምሮ ዕድሜያቸው ከ5ዓመት በታች የሆነ ከ47584 በላይ ህጻናት ክትባት እንዲያገኙ ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የፖሊዮ በሽታ (ልጅነት ልምሻ) በዓይን በማይታይ የፖሊዮ ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ መሆኑ የገለፁት አቶ አባይነህ በሽታው የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት የእጅ፣ የእግር ወይም ሁለቱንም እጅና እግርን የሚያዝለፍለፍና ዘላቂ የሆነ ሽባነት እንዲሁም ሞትን የሚያስከትል በሽታ ነዉ ብልዋል።
የፖሊዮ በሽታን መከላከል የሚቻለው ህፃናትን በመደበኛ የክትባት መርሃ ግብር እና በዘመቻ የሚሰጠውን ሁለት ጠብታ የፖሊዮ የማጠናከሪያ ክትባት በአግባቡ እንዲከተቡ በማድረግ ነው።
አክለዉ በዞናችን ለሁሉም እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ከአሁን በፊት ቢከተቡም ባይከተቡም የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጣቸው ተናግሯል።
የመምሪያው የድንገተኛ አደጋ ቅኝት እና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ሃይሉ በበኩላቸው የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በዞኑ በሁሉም አካባቢ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ክትባቱ ቤት ለቤት እና በመዋለ ህፃናት ትምህርት ቤት ደረጃ ለሁሉም ከ5 አመት በታች ለሆኑ ህፃናት በአፍ በጠብታ መልክ በሰለጠኑ ጤና ባለሙያዎች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ከፖሊዮ ዘመቻ ጋር በቅንጅት የቆልማማ እግር ልየታ እና ከዚህ ቀደም ክትባት ያልጀመሩና ክትባት ጀምረዉ ያቋረጡ ከ5 አመት በታች ህፃናት ሁሉንም የመደበኛና ማካካሻ ክትባት በተመረጡ የክትባት መስጫ ጣቢያወች በቅንጅት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በመደበኛ እና በዘመቻ መልክ የሚሰጠዉን የፖሊዮ መከላከያ ክትባት በማስከተብ ህጻናትን ከልጅነት ልምሻ በሽታ መታደግ አለባቸው ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በስልጠና መድረክ ላይ የዞን ፣ የወረዳ እና የከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዘገባው የምዕራብ ኦሞ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው::