በእናቶችና ህፃናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ለጋሽ ድርጅቶች የጤና ተቋማትን በልዩነት በመደገፍ በእናቶችና ህፃናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር ለመቀነስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ውይይት በሲዝ ከተማ ተካህዷል።
በዶ/ር ማርጋሪት የተመራ አለማቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅት በሲዝ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ጉብኝት ባደረገበት ወቅት የሲዝ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ አዲሱ አገራሻ እንደተናገሩት አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ለጋሽ ድርጅቶች የጤና ተቋማትን በልዩነት በመደገፍ በእናቶችና ህፃናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር ለመቀነስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
የከንቲባ ተወካዩ ባስተላለፉት መልዕክት “ቪሌጅ ሄልዝ ፓርትነርሺፕ” የተባለው አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ደርጅት ከአፍሮ ኢትዮጵያ ኢንተግሬት ዴቨሎፕመንት ጋር በመሆን የሲዝ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን አቅም ለማሳደግና አሁን ያለበትን የህክምና ቁሳቁስና ሌሎች የግብዓት ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ ጉብኝት በተደረገበት ወቅት እንደተናገሩት ለጋሽ ድርጅቶች የማህበረሰቡን የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ድርጅቱ በመሰረታዊነት የንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ በእናቶችና በህፃናት ጤና እንዲሁም በሆስፒታል አካቢቢዎች የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት በማድረግ የሚሰራ አለማቀፍ ድርጅት እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በሲዝ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ያለበትን የቁሳቁስ እጥረት በመለየት በርካታ ድጋፎችን እያደረገም ይገኛል።
የሆስፒታሉን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን የተመለከተ ገለፃ ያደረጉት ዶ/ር ይትባረክ እንደገፁት ሆስፒታሉ በከተማ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ወረዳዎችና ለአጎራባች ዞኖች አገልገሎቶች እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በሆስፒታሉ በቂ የአንቡላንስ፣ የቀዶ ጥገና ማሽን፣ የእናቶችና ህፃናት ማቆያ ና ሌሎችም የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት መኖሩን የገለፁ ሲሆን ዶ/ር ይትባረክ አያይዘውም ከህክምና አገልግሎቱ በተጨማሪ ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ችግሮች በሆስፒታሉ ላይ የተሟላ አገልግሎት እንዳይሰጥ እንቅፋት እንደሆነበት ተናግሯል።
ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የውሃ አገልግሎትን ለማሟላት የሶላር ማሽን ድጋፍ በማድረጉ የሆስፒታሉንና የአካባቢውን የንፁህ ውሃ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ድጋፍ የተደረገለት መሆኑም ይታወቃል።
አለማቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የሆስፒታሉን ችግሮች ለመቅረፍና አሁን ያለበትን የአገልግሎት ነባራዊ ሁኔታ የተመለከተ ጉብኝት ሲያደርጉ የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ጎበዜ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን ሆስፒታሉ ያለበትን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ደረጃ ለማሻሻል የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ዘገባው የሲዝ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።