በካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሸራዳ ጤና ጣቢያ ተመረቀ::
የጤና ጣቢያውን መርቀው የከፈቱት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው ።
ምክትል ርዕሠ መስተዳድሩ ጤና ጣቢያው ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት በመደረጉ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈው የጤና ጣቢያው ስራ መጀመር የአካባቢውን ህብረተሠብ የጤና አገልግሎት እንደሚያሻሽለው አብራርተዋል::
የተመረቀው ጤና ጣቢያ ለአካባቢው ሕዝብ የልማት መነሻ ነው ያሉት አቶ ማስረሻ ተጀምሮ ሳይመረቅ የቆየው ጤና ጣቢያ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እንዲገባ በየደረጃው ያሉ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል::
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው በክልሉ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎች እየተሰራ ነው ብለዋል::
በተለይም የእናቶችን እና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ እንዲሁም አንድም እናት በወሊድ ምክንያት ህይወቷን እንዳታጣ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የበኩላቸውን አበርክቶ እየተወጡ ያሉ የጤና ጣቢያዎችን ቁጥር ዛሬ የተመረቀውን ጨምሮ 125 ጤና ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
የጤና ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንዲሁም የእናቶችና ህፃናትን ሞት መቀነስ የሚቻለው የጤና መሰረተ ልማቱን ተደራሽ በማድረግ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው ከነሱም አንዱ ዛሬ የተመረቀው የሻራዳ ጤና ጣቢያ አንዱ መሆኑን አንስተዋል::
የጤና አገልግሎት ተቋማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን በውስጣቸው መሟላት ያለባቸውን የህክምና መሳሪያዎች ማሟላት ላይ መሰራት እንዳለበት ያነሱት አቶ ኢብራሂም እነዚህን የህክምና መሳሪያዎች ለማሟላት ክልሉ ከፌደራል ጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እየሰራ ነው ብለዋል::
የቢሮ ኃላፊው አክለዉም የክልሉ ጤና ቢሮ ሌሎች ዘርፉን ከሚደግፉ አጋር አካላት ጋር በመሆን የህክምና መሳሪያዎችን ለማሟላት ይሰራል ብለዋል::
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው በአካባቢው በተደጋጋሚ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ጤና ጣቢያ በመሆኑ ብልጽግና ፓርቲ በሰጠው ትኩረት መመለስ መቻሉን አንስተዋል::
የተመረቀው ጤና ጣቢያ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ዞኑ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል::
የአዲዮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገረመው ገብሬ በበኩላቸው የጤና ጣቢያው መመረቅ በሸራዳና አካባቢው ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል::
የተመረቀው ጤና ጣቢያ ሸራዳን ጨምሮ በኮሻና መዱጣ ቀበሌዎች የሚገኙ 28 ሺ በላይ ነዋሪዎችን እንደሚያገለግል ገልፀዋል::
በወረዳው 5 ጤና ጣቢያዎችና አንድ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መኖሩን የተናገሩት አቶ ገረመው ዛሬ የተመረቀው ጤና ጣቢያ ከነሱ አንዱ መሆኑን አብራርተዋል::
ብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱን ማስተዳደር የጀመረመበት 5ተኛ ዓመት የሚከበርበት ወቅት ላይጤና ጣቢያው መመረቁ ዕለቱን ልዩ ያደርገዋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ዛሬ የተመረቀው ይህ ጤና ጣቢያ የወረዳዉን ጤና አገልግሎት ሽፋን ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል::
ጤና ጣቢያው የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ከ3ቱም ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር ዉይይት በማድረግ ከ 8 መቶ ሺ በላይ ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል::
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የክልልና የዞን የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎችና ተወላጆች ጤና ጣቢያውን ለማስጀመር የገንዘብና ሌሎች ድጋፎችን አበርክተዋል::
ከጤና ጣቢያው መመረቅ ጋር ተያይዞ የሸራዳ ቀበሌ የመብራት አገልግሎትም ተጠቃሚ መሆን ችላለች ::
የተመረቁት እነዚህ ተቋማት እና የመሰረተ ልማት ስራዎች የአካባቢው ነዋሪዎችን የዘመናት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምላሽ የሰጡ መሆናቸው በዚሁ ጊዜ ተገልጿል ::
ዘገባው የካፋ ማህበረሰብ ቴሌቪዥን ነው