በካፋ ዞን ከ49 ሺህ በላይ ልጃ-ገረዶችን ተደራሽ የሚያደርግ የማህፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት መሰጠት ተጀመረ፡፡
ክትባቱ በቦንጋ ከተማ ሸታ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ ነው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የተጀመረው፡፡
በማስጀመሪያ መርሃግሩ ላይ የተገኙት የካፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር ለሴቶችና ህፃናት መሞት ምክንያት ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ዕድሜያቸው ሳይደርስ የግብረስጋ ግኑኝነት የሚፈፅሙ ልጃገረዶች ላይ የበሽታው የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ይህ ክትባት ወደፊት በተጠቀሰው ምክንያት የማህፀን ጫፍ ካንሰር እንዳይዝ ለመከላከል ታልሞ የሚሰጥ እንደሆነ ጠቁመው፣ ሁሉም ዕድሜያቸው የደረሱ ልጃገረዶች ይህን ክትባት መወሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የሚሰጠው ክትባት ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደማያስከትልም ነው አቶ አክሊሉ የገለጹት፡፡
በካፋ ዞን ደረጃ ዕድሜያቸው ከ 9 እስከ 14 ዓመት የሚገኙ ከ49 ሺህ በላይ ልጃገረዶች ይህን ክትባት እንደሚከተቡም ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የክትባቱ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዮሐንስ አዘዘው፣ እንደ ሀገር ከ6 መቶ ሺህ በላይ እናቶች ልየታ እንደሚደረጉና ከዚህም ወደ 5 መቶ ሺህ የሚሆኑት ለበሽታው ተጋላጭ መሆናቸውን ይገልፃሉ፡፡
እንደ ክልል ከ 1 መቶ 57 ሺህ በላይ ልጃገሰዶችን ለመከተብ መታቀዱን ጠቁመው፣ ክትባቱን የሚወስዱ ሴቶች ከበሽታው ይጠበቃሉ ብለዋል፡፡
የቦንጋ ከተማ ጤና ጽ/ቤት የእናቶችና ህፃናት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጌታቸው ሃይሌ፣ በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሴቶች ሞት ምክንያት በ2ኛ ደረጃ የተቀመጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ክትባቱ በትምህርት ቤትና ከትምህርት ቤት ውጪ ለሚገኙ ልጃገረዶች እንደሚሰጥና ለረጂም ዓመታት በሽታውን የመከላከል አቅም ያለው ነውም ብለዋል፡፡
ክትባቱን እየወሰዱ ከሚገኙ ተማሪዎች መካከል ያነጋገርናቸው ተማሪ ሰሎሜ ፀጋዬ እና ትንቢት መሃመድ፣ በሽታው ብዙ እናቶችን የሚያጠቃ በመሆኑ ክትባቱን መውሰዳችን ጠቄሜታ አለው ብለዋል፡፡
ልጆች በዚህ አስከፊ በሽታ እንዳይጠቁ ወላጆች ክትትል በማድረግ ካለዕድሜ ግብረስጋ ግኑኝነት እንዲቆጠቡ ማድረግ አለባቸው ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ዕድሜያቸው ከ9 ዓመት እስከ 14 ዓመት ድረስ ለሚገኙ ልጃገረዶች በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት፣ እና በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ከህዳር 9 እስከ ህዳር 14 ቀን 2017 ዓ/ም ይሰጣል፡፡