በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት ሥራዎች ላይ ያለዉን አፈጻጸም በፍጥነት ማሻሻል ይገባል። ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር)::
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሚዛን አማን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ2017 በጀት ዓመት ክልላዊ ማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።
ክልላዊ የንቅናቄ መድረኩ ”የጤና መድህን አገልግሎት ለጋራ ተጠቃሚነት”በሚል መሪ ቃል ነው በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው።
የክልሉ ርዕሰ መስተደድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በመድረኩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት ሥራዎች አፈጻጸም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎችን ቢያሳይም ከሚጠበቀዉ ዉጤት አኳያ አፈጻጸሙ አነስተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና መድህን አገልግሎት ስራ ለህብተረሰባችን ወሳኝ ጉዳይ ስለሆነ አባላትን ማፍራት እና ነባር እድሳት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ይህ ሥራ በተለየ ትኩረት መርቶ ዉጤት ማምጣት ይጠበቃል ስሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቀጥሎ ባለዉ ጊዜ ሁሉንም የጤና መድህን ተግባራት ሙሉ በሙሉ መፈጸም ይጠበቃልም ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው የማህበረሰብ ዓቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ማህበራዊ ብልጽግናን ከሚያረጋግጡ ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ በ48 የማዕጠመ ቋት እና በ60 ወረዳዎችና ከተማ አስተደደሮች የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ 300 ሺህ 51 አባላት ማፍራት መቻሉን ኃላፊዉ ተናግረዋል።
በ2016 በጀት ዓመት 292 ሺህ 943 አባላትና ቤተሰቦቻቸው በጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን የህክምና አገልግሎት ለሰጡት ጤና ተቋማትም 102 ሚሊዮን 265 ሺህ 574 ብር መክፈል መቻሉን አቶ ኢብራሂም ገልጸዋል።
በዚህም የማዕጠመ አባልነት መዋጮ መክፈል የማይችሉ 71 ሺህ 131 ዜጎችን መመልመል መቻሉንም ያብራሩት የቢሮ ኃላፊው በክልሉ በ2017 ዓ.ም ነባር የአባላት ዕድሳትና አዲስ አባላት ማፍራት ስራ ተጀምሮ እየተሰራ ሲሆን ያለው ጊዜ አጭር በመሆኑ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በየደረጃው የሚገኙ አካላት መረባረብ ይጠበቃል ብለዋል።
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዳይሬክተሮች እንዲሁም ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸው የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የ2017 ዓ.ም የማዕጠመ አፈጻጸ ሰነድ ቀርቦ ዉይይት እየተደረገበት ይገኛል።