በክልላችን በሁሉም አካባቢዎች የፖሊዮ መከላከያ ክትባት ዘመቻ በተጠናከረ መንገድ ይሰጣል።
በክልል አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ከየካቲት 14-17/06/2017 ዓ.ም እንደሚሰጥ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በሰጡት መግለጫ በዘመቻዉ 552 ሺህ 246 ዕድሜያቸዉ ከ5 ዓመት በታች ለሚሆኑ ህፃናት ተደራሽ እንደሚደረግ አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል ።
የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዉም የሚካሄደዉ ቤት ለቤት መሆኑንም የገለጹት የቢሮ ሀላፊው ዕድሚያቸዉ ከ5 አመት በታች የሆኑ ክትባት ያልጀመሩ እና ጀምረዉ ያቋረጡ ልጆች የመለየትና የመከተብ ስራ ተቀናጅቶ እንሚሰራ አቶ ኢብራሂም አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የሚደረገዉ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በአለም እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ የተያዘዉን ፖሊዮን የማጥፋት ስራ የሚያጠናክር ክትባት መሆኑንም አቶ ኢብራሂም አብራርተዋል፡፡
ዘመቻዉን በጥራት ለታላሚዎቹ ተደራሽ ለማድረግ በየደረጃዉ ያለዉን ባለሙያ የማሰልጠንና ስምሪት የመስጠት እንዲሁም የግባት ስርጭት ስራ በትኩረት ተይዞ እየተሰራ ሲሆን በየደረጃዉ ያለዉ የጤናዉ ሴክተር አመራርና ባለሙያ ይህ ዘመቻ በተያዘዉ ጊዜ ጥራቱን ጠብቆ በሚጠበቀዉ ሽፋን ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት እንዲመራ የቢሮ ሀላፊ አሳስበዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች ፣የሀይማኖት አባቶች እና ባለድርሻ አካላት እና በየደረጃዉ ያሉ የአመራር አካላት የክትባት ዘመቻዉ ዉጤታማ እንዲሆን የድርሻቸዉን እንዲወጡ ጠይቀዋል አቶ ኢብራሂም ።
በዚህ ወር መጨረሻ የሚጠናቀቀውም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን (ማዐጤመ) መዋጮ በሁሉም የክልላችን ቀበሌዎች የተቀመጠውን ግብ በማሳካት የአባላት ምጣኔን ማሻሻል ይጠበቅብናል ሲሉም አቶ ኢብራሂም በተጨማሪም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡