በኮንታ ዞን የወባ ወረርሽኝ ለመግታትና ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል እየተሰሩ ያለው ስራዎች ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለፀ።

በደ/ም/ዕ/ኢ/ሕ/ክ/መንግስት ጤና ቢሮ በኮንታ ዞን የወረዳና ከተማ አስ/ር መዋቅር ሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር የወባ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ አፈፃፀም ላይ የጋራ ምክክር መድረክ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ምክትል አፌ-ጉባኤ ወ/ሮ ፀሀይ ዳርጫ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ እያስከተለ ያለውን ጫና ለመቆጣጠር ሁሉም የባድርሻ አካላት የሁልጊዜ የትኩረት ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የአመራር አካላት በተቀናጀና በተደራጀ መልክ የወባ ወረርሽኝን የመከላከል ስራ ላይ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የኮንታ ዞን ም/ል አስተዳዳሪና ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ወጁ እንደገለጹት የወባ ወረርሽኝ በሽታ ለመቆጣጣርና ለመከላከል ህብረተሰቡን በግንዛቤ በማንቃት በዞኑ ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል በየደረጃው የሚገኝ አመራር በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በት/ቤቶች፣ በሀይማኖት ተቋማትና በመሳሰሉ ቦታዎች ከህብረተሰቡ ጋር ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የኮንታ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ እንግዳወርቅ ዶኖቾ በበኩላቸው ወረርሽኙን በዘላቂነት ለመግታት የሚደረገው ርብርብ ባለድርሻ አካላትና ጤና ባለሙያዎች ከአመራር አካላት በመቀናጀትና በመግባባት ዕቅድን በተገቢው መፈጸም እንደሚገባ ገልፀዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክተር ዶክተር እንዳለ ሳህሌ እንዳነሱት ወቅቱን ተከትሎ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ሊሰራጭ ስለሚችል የቁጥጥር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
እንደ ዞን የወባ ወረርሽኙን በዘላቂነት ለመግታትና ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሰሩ ያለው ስራዎች አበረታች መሆናቸውንም አንስተዋል።
በመድረኩ የማኔጅመንት አባላት እና ከፍተኛ ባለሙያዎች እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ቡድን በሁሉም መዋቅሮች እስከ ቀበሌ ድረስ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈን፣ የማፋሰስ እና የአልጋ አጎበርን በአግባቡ በመጠቀም ወረርሽኙ ሊያስከትል ያለውን ጫና ለመቀነስ ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠትና ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ ተጠቅሷል።
በዞኑ የሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በማነቃቃትና የህብረተሰብ ተሳትፎ በማሳደግ በርብርብ ሊሰራ ይገባልም ተብሏል።
ዘገባው የኮንታ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው።