በዘላቂነት በወርሽኝ መልክ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል እና መቆጣጠር ህክምና ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን ቀድሞ መከላከልን መሰረት አድርጎ መስራት ጠቃሚ እንደሆነ ተገለጸ።

የደቡብ ም/ኢ/ህ/ክ/መ ጤና ቢሮ እና የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ በሽታዎች ድጋፍና ክትትል ቡድን አባላት በዛባ ጋዞ ወረዳ አንገላ ጤና ጣቢያ ተገኝተው ድጋፍ አድርገዋል።
የደ/ም/ኢ/ህ/ክ/መ/ጤና ቢሮ ጤና እና ጤና ነክ ግብዓት ቁጥጥር ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አሰፋ በዘላቂነት ህብረተሰቡን ከወባ ጫና ስጋት ለማዳን መከላከል ላይ መሰረት አድርጎ መስራት ብቸኛ አማራጭ ነው ብለዋል።
በዛባ ጋዞ ወረዳ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የክልሉ ጤና ቢሮ የተቻለውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው የሚሰጠው ድጋፍ ውጤት ማስመዝገብ የሚችለው የሁሉም አካላት ትብብር ሲታከልበት ብቻ ነው ብለዋል።
ወባ እና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የተሳሳተ አመለካከት ሊቀረፍ የሚችለው የጤና ባለሙያዎች ያልተቆራረጠ የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት ነው ብለዋል።
በተለይ በዳሻ አጃ ቀበሌ የታየው የኩፍኝ በሽታ ወደሌሎች አጎራባች አካባቢዎች በመዛመት በህጻናት ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ምንም ክትባት ያልወሰዱትን ህጻናትን በመለየት ክትባት መስጠት እና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችና የጤና ጣብያ ባለሙያዎች ህብረተሰብ ውስጥ በመውረድ በሽታ የመከላከል እና የመቆጣጠር ስራን በተጠያቂነት መተግባር ይጠበቃል ብለዋል።
ለወባ እና ለኩፍኝ ህክምና አገልግሎት የሚውሉ የላቡራቶር ሪጀንት፣ ማይክሮስ ኮኘ ስላይድ፣ ቫይታሚን ኤ፣ አሞክሳስሊን ፣ቴትራ ሳይክሊን እና ሌሎች መድሀኒቶች እና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው ግብአቶቹ ለታለመለት ዓለማ ማዋል ይገባል ብለዋል አቶ ሙሉቀን።
የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አስራት ቸርነት በዛባ ጋዞ ወረዳ የህብረተሰብ ጤና ስጋት የሆኑ በሽታዎች ተደጋግሞ በተከሰተባቸው በዳሻ አጃና አካባቢው ተተክለው እንዲሰሩ በውሳኔ የተቀጠሩ የጤና ባለሙያዎች ፈጥነው በተቀጠሩበት ቦታ ላይ ተገኝተው ስራ መጀመር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
አሁን የመከላከል ስራ ላይ መቀዛቀዙ እንዳለ የጠቀሱት የወረዳው ጤና ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ተመስገን ሰብሮ ለወባ ትንኝ መራቢያ ሆነው የተለዩት ቦታቦች በህብረተሰብ ተሳትፎ የማዳፈንና የማፋሰስ እንዲሁም አጎበርን በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በጤና ተቋማት የሚታየውን የመገልገያ ግብዓትና መድሀኒት እጥረት ለማቃለል እየሰሩ እንደሆነ ገልጸው ለአንገላ ጤና ጣቢያ በክልልሉ ቢሮ እና በዞኑ ጤና መምሪያ በኩል ለተደረገላቸው የመድሀኒት ድጋፍ አመስግነዋል አቶ ተመስገን።
የአንገላ ጤና ጣቢያ ሀላፊ አቶ አበጀ አታሮ በአንገላ ጤና ጣቢያ ክላሰተር በሚገኙ 9 ቀበሌዎች 921 ጊዚያዊ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎች እንደተለዩ ገልጸው እነኝህ ቦታዎችን የማዳፈንና የማፋሰስ ስራ በህብረተሰብ ተሳትፎ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ሁሉንም የክትባት አይነቶች ለመስጠት እንደሚሰሩም የገለጹት አቶ አበጀ አታሮ አሁን ላይ ከ2,000 በላይ ህጻናት መከተብ የሚያስችል ግብዓት የተመቻቸላቸው መሆኑን ገልጸው ከተላከው ክትባት 670 ህጻናትን መከተባቸውን ገልጸዋል።
የድጋፍና ክትትል ውስጥ የተሳተፉ የቡድን አባላትም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ የመከላከል ስራ ላይ ጠቃሚ ምክርና አስተያየት ሰጥተዋል።