በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ምጣኔ 0.65 ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ
የክልሉ ጤና ቢሮ ለሴክተር መስሪያ ቤቶችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤች .አይ.ቪ ሜይንስትሪሚንግ ላይ በቦንጋ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል።
ለሴክተር መስሪያ ቤቶችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሜይንስትሪምንግ ላይ የተሰጠው ስልጠና ኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት መከላከልና መቆጣጠር ላይ ግንዛቤ የሚያሳድግ እንዲሁም ተቋማት ተግባሩን የዕቅድ አካል በማድረግ በባለቤትነት እንዲመሩ የሚያስችል መሆኑም ተመላክቷል።
በስልጠናው ማጠቃለያ የክልሉ ጤና ቢሮ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ከሰሪ እንዳሉት የስርጭቱ ምጣኔ ደረጃ ቢለያይም በክልሉ በሁሉም ዞኖች የቫይረሱ ስርጭት እንዳለና የስርጭቱ ምጣኔ 0.65 ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በክልሉ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቫይረስ የስርጭት ምጣኔ 0.65 ደረጃ ላይ መኖር በከፍተኛ ሁኔታ የስርጭት መስፋፋት እንዳለ አመልካች ነው ብለዋል።
በክልሉ ሚዛን አማን፣ቦንጋ፣ቴፒ ከተማ ፣ቤሮና ማጂ ወረዳዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭቱ ጫና ከሚያሳድርባቸው ከተሞች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።
ዳይሬክተሩ ክልሉ የልማት ኮሪደር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቫይረሱ ስርጭት መጠን እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑንና ጥንቃቄ የጎደለው የግብረስጋ ግንኙነቶችና ሌሎች ችግሮች ለስርጭቱ መስፋፋት መንስኤ እንደሆናቸውም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል።
በክልሉ 6ቱ ዞኖች 38 የጸረ-ኤድስ ህክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት መኖራቸውን አንስተው ከተቋማት ጋር በመሆን በደማቸው ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች መድሀኒት እንዲወስዱና የህክምና ሂደታቸውን መከታተል እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በጤና ተቋማት ብቻ የቫይረሱን ስርጭት መግታት የማይቻል በመሆኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፤የትምህርትና የኃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሁሉም ማህበረተሰቡ ክፍሎች የጋራ ርብርብ እንዲያደርጉ አመልክቷል።
ሰልጣኞቹ ተግባሩን የተቋማቸው የእቅድ አካል ተደርጎ እንዲሰራ፤ ከመንግስት ሰራተኞች የሚቆረጠው የ0.5 በመቶ የኤድስ ፈንድ ለታለመለት አለማ እንዲውልና በየተቋማት የተቀዛቀው የሜንስትሪምንግ ውይይት በማጠናከር ላይ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ገልጸዋል።
በየተቋማት የኤች አይ ቪ ኤድስ ሜንስትሪምንግ መደብ ላይ ተመድበው ስራውን በባለቤትነት መስራት እንዳለበትና የሚቆረጠው የአድስ ፈንድ በተከፈተው አካውንት ላይ ገቢ በመሆን ለቫይረሱ ተጠቂዎች ተደራሽ እንዲሆን መሰራት እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል።