በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ለሚገኙ ጤና ባለሙያዎች የሙያና ስራ ፈቃድን በበይነ መረብ (Digital system) ለመስጠት የሚያስችል ማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ።
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር እና የባለሙያዎች ፈቃድ አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱልአዚዝ ፈረጃ እንደገለጹት የጤና ባለሙያዎች ከሚሠሩበት አካባቢዎች ሳይርቁ የሙያ ፈቃድን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻላቸው አላስፈላጊ እንግልት የሚያስቀር ነው።
ከዚህ ቀደም ባለው የአሠራር ሥርዓት በአካል ወደ ክልል ጤና ቢሮ ድረስ በመገኘት በጊዜ፣ በገንዘብና በጉልበት መባከን ላይ ሲደርስ የነበረውን እንግልት እንደሚያስቀርላቸውም ተገልጿል።
ከዚህ በኋላ ከሚሠሩበት ዞን የጤና መምሪያ የሰው ሃብት አስተዳደር ተገቢ መመሪያ በመውሰድ ከሚሠሩበት የጤና ተቋም ሳይነቀሉ ፈቃድ ማግኘት እንደሚችሉ ነው የተብራራው።
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አሰፋ በበኩላቸው ከመስከረም 27/2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ክልል ጤና ቢሮ በአካል ሳይገኙ የሙያ ፈቃድ ማደስም ሆነ አዲስ ፈቃድ የሚፈልጉ ባለሙያዎች ማግኘት እንደሚችሉ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ መልካም ዕድል መሆኑን ለተሳታፊዎች አስረድተዋል።
አያይዘውም ባለሙያዎቹ ተረጋግቶ በመሥራታቸው የጤና ተቋሙ በሽታን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ተገልጿል ።
በክልሉ 2 ሺህ 76 የጤና ተቋማት የሚገኙ ሲሆን የክልሉንና የአጎራባች ክልል ነዋሪዎችን በጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በትኩረት እየተሠራ እንዳለም ይታወቃል።
ከዚህ በኋላ በgoogle ውስጥ https;//hrl.moh.gov.et በማለት በsign up አዲስ email በመክፈት መልሶ በlog in የሚጠየቁ ማለፊዎችን በማለፍ መመዝገብ ፈቃድ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።