በዳውሮ ዞን በሁሉም ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ።

የደቡብ ም/ኢ/ህ ክልል ጤና ቢሮ ድጋፍና ክትትል ቡድን አባላት በዳውሮ ዞን የወባ ወረርሽኝ የመከላከል ዘመቻ አፈጻጸምና ቀጣይ ተግባራት ላይ ከዞኑ ጤና መምሪያ ማኔጅመንት አባላትና ባለሙያዎች ጋር በታርጫ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
የድጋፍና ክትትል ቡድኑን የመሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ጤና እና ጤና ነክ ግብዓት ቁጥጥር ባልስልጣን ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አሰፋ ባለፉት ወራት በወባ ወረርሽኝ መከላከል ላይ የተሰሩ አበሰታች ተግባራት ቢኖሩም በዞኑ በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ለመከላከሉ ስራ ውጤታማነት የጤና ኤከስተንሽን ኘሮግራም ማጠናከር ቁልፍ ሚና ይጫወታል ያሉት ሀላፊው ሁሉም ጤና ኬላዎች ክፍት ሆነው ለህብረተሰቡ አገልግሉት የሚሰጡበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።
በዞኑ የኩፍኝ በሽታ ምልክት በታየባቸው በዛባ ጋዞ እና ኢሰራ ወረዳዎች የመከላከሉ ስራ መሰራት እንዳለበት ገልጸው ወደ ሌሎች ወሰዳዎች እንዳይተላለፍ በቅንጂት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አስራት ቸርነት ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች በዞኑ የህብረተሰቡ የጤና ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል በቀጣይ ከዞን ፣ከወረዳ፣ ከቀበሌ እና ከሌሎች ባልድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል።
መረጃን አደራጅቶ ከመላክ ጋር ያለውን ውስንነት ለመፍታት የተሰራው ስራ ለውጥ አምጥቶ የነበረ ቢሆንም አሁንም ለቅሞ ከመስራት አንጻር የሚታየውን ክፍተት በሚታረምበት መንገድ ላይ እንሰራለን ብለዋል።
ለህብረተሰቡ የተላከው የህክምና ግብዓት ክትትልና ቁጥጥር ስራ በአንድ ወገን የሚሰራ ተግባር ሳይሆን ሁሉም አካላት በተቀናጀ መንገድ በመስራት አንድም ታካሚ በመድሀኒትና መገልገያ ቁሳቁስ ምክንያት እንዳይጉላላ መሰራት ይገባል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎችና አመራሮች ከወባ ወረርሽኝ ዘመቻ ስራ ባሻገር ሌሎች የጤና ተግባራትን በማጠናከር የተጀመረውን የወባ መከላከል ዘመቻውን አጠናክሮ መሄድ እንደሚገባ በውይይቱ ተጠቁሟል።
ከቀረበው ሪፖርት መነሻ የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየትና ጥያቄ አቅርበው አሁንም ቢሆን የመከላከሉን ስራ አጠናክረው ለማስቀጠል ወደ ጋራ መግባባት ተደርሷል።
በመድረኩ የወባ ወረርሽኝ የመከላከል ዘመቻ አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በስፋት ውይይት ተደርጎ መድረኩ ተጠናቋል።