በጤና ዘርፍ ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት ባለሙያዎች በክህሎታቸው የዳበሩና ሙያዊ ስነ-ምግባር የተላበሱ መሆን እንደሚገባ ተገለጸ።

የጤና አገልግሎት ጥራት ማሻሻል እና የህክምና ተግባቦት ክህሎት ስልጠና ለጤና ጣቢያዎች እና ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ባለሙያዎች በታርጫ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።
የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር እንዳለ ሳህሌ እንደገለጹት በጤና ዘርፍ ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ባለሙያዎች በክህሎታቸው የዳበሩና የሙያዊ ስነ-ምግባር የተላበሱ መሆን አለባቸው።
የጤና ባለሙያዎች ክህሎታቸውን አዳብረው አገልግሎታቸውን በፍትሀዊነት ተደራሽ እንዲያደርጉ ለማስቻል እየተሰጠ ያለው ስልጠና ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ዶክተር እንዳለ ተመሳሳይ ስልጠና ለሁሉም ጤና ባለሙያዎች በተከታታይ ይሰጣል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ኤከስቴንሽን ኘ/የመ/ደ/ጤ/አሀድ ባለሙያ እና የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ተክሊት ተስፎም ስልጠናው የጤና አገልግሎት ጥራት እና ተግባቦት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሰጠት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ለ5 ተከታታይ ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ከሁሉም ዞኖች የጤና ጽ/ቤት እና ከተመረጡ ጤና ጣቢያዎች የተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።