አስፈፃሚ ተቋማት በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛል።
እየተካሄደ በሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የአስፈጻሚ ተቋማት ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በዚህም አጋር የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር በገጠር መሬት መረጃ አያያዝ፣ ቴክኖሎጂ ስርፀትና ስርጭት ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን አብራርተዋል።
የግብርና ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ ያለውን ከፍተኛ የአሲዳማ አፈር ለማከም ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ማስረሻ እያደገ የመጣውን የምርጥ ዘር ፍላጎት ለማሟላት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ ‘በኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን’ ለአርሶአደሮች ተሞክሮ ለማስፋት ትኩረት መሰጠቱን ነው የጠቆሙት።
በክልሉ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ የመቆጣጠር ስራ በከፍተኛ የህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ‘የጤና ኤክስቴንሽን’ ስርዓትን በማጠናከር እንዲሁም የምርመራና ህክምና አግልግሎት በማሻሻል ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።
በሁለት ወራት ውስጥ 432,488 የወባ ታማሚዎችን የሚያክም መድሀኒት በሁሉም ወረዳዎችና ጤና ተቋማት ተደራሽ መደረጉን የቢሮ ኃላፊዉ ገልጸዋል።
የመደበኛ ጤና አግልግሎት አፈጻጸምም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር መሻሻል እያሳየ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢብራሂም በመድኃኒት አቅርቦት፣ አስተዳደርና ቁጥጥር ሥራ በልዩ ትኩረት በመደረጉ ህገወጥነትን በተጨባጭ የመከላከል ስራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
ግንባታቸው በፌዴራል መንግሥት ተጀምሮ የቆሙ መንገዶችን በሚመለከት ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ ምላሽ እየተጠበቅ መሆኑን የገለጹት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በክልሉ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ በሚከሰትበት የቀነች አከባቢ የመንገድ ዲዛይን ለውጥ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
በገጠር ተደራሽ መንገድ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በርካታ የመንገድና የድልድይ ግንባታ በበጀት ዓመቱ ማከናወን መቻሉን የገለጹት አቶ ፋጂዮ ሳፒ በመንገድ ጥገና ስራዎች ረገድም ውጤታማ ስራዎችን መስራት መቻሉን ገልጸዋል።
ዘገባው የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።