ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነው ወጪ የተገነባው የማህበረሰብ ሞዴል መድኃኒት ቤት በይፋ ተመረቀ

የካፋ ዞን ዋና እስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ እንዳሉት ዘርፍ የማህበረሰቡን ጤና ለማስጠበቅ መንግስት ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ቢሆንም የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ለዘርፉ ዉጤታማነት ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።
መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የሞዴል ፋርማሲዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ለተግባራዊነቱ የቦንጋ ገብረ ጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ያደረገዉ እንቅስቃሴ የሚመሰገን ነዉ ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ ቅሬታዎች እንዳይደገሙ በተገልጋዩ ዘንድ በስፋት የሚፈለጉ መድሃኒቶችን ያለማቋረጥ ለማቅረብ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ለዚህም የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም እንደተናገሩት በክልሉ ባለፉት 3 ወራት ወደ 6 የሚጠጉ የማህበረሰብ አቀፍ ሞዴል የመድኃኒት መደብሮች
በሆስፒታሎች ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።
በዚህም የቦንጋ ገ/ጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል በአስፈላጊ ግብዓቶች እና በተደራጀ የሰዉ ሀይል ይህን ተግባር በመከወኑ የመድሃኒት አቅርቦች ችግርን በመቅረፍ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያደርገው እንቅስቃሴዎችን በብዙ መልኩ የሚደግፍ ነዉ ብለዋል።
ለዚሁ ተግባር ምስጋና ያቀረቡት አቶ ኢብራሂም ፋርማሲዉ የመገንባቱ ዋነኛው አላማ የማህበረሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ የመድሃኒት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጾኦ የሚያበረክት በመሆኑ የሚመለከታቸዉ አካላት ሊደግፉ ይገባል ብለዋል ።
በተለያዩ ጊዜያት የሚደረጉ ህዝባዊ ዉይይቶች ላይ በሆፒታሉ የሚስተዋለዉ የመድሃኒት አጥረት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱን የገለጹት አቶ ኢብራሂም የተከፈተዉ ሞዴል ፋርማሲ በራሱ የፋይናንስ ስርዓት የሚተዳደር መሆኑ ችግሩን ያቀለዋል ብለዋል ።
የክልሉ ጤና ቢሮ የመድሃኒት አቅርቦት እና የበጀት ችግሮችን ለመቅረፍ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ ይህንን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ዞኖችና ወረዳዎች ማስፋት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የካፋ ዞን ጤና መምርያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ መድሃኒት ቤቱን ከለላው ለየት የሚያደርገው በህዝቡ ፍላጎት መሠረት መሟላት ያለባቸው መድኃኒቶችን የማሟላት ስራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመድኃኒት ቤት የመልካም አስተዳዳር ችግር ከመፍታት ባሻገር የህዝቡ እርካታ ማሳደጉ ትልቅ ተስፋ እንደሰጣቸው ገልፀዋል።
የገብረ ጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅረማርያም ጳዉሎስ በበኩላቸዉ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገዉን መድሃኒት እንድያገኝ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ የሚነሱ ሃሳቦች መሆናቸዉን በመግለጽ ሌሎች አካባቢዎች ያሉ ተሞክሮዎችን በመቅሰም ይህ ተግባር መከዉኑን አንስተዋል።
ይህ ተግባር ከግብ እንዲደርስ የተለያዩ አካላት ድጋፍ ማድረጋቸዉን የገለጹት አቶ ፍቅረማርያም ማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚፈልገዉን አገልገሎት እንድያገኝ ሆስፒታሉ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ ሞዴል ፋርማሲውን ለማስገንባት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ሀላፊው ተናግረዋል፡፡
ተጠቃምዎችም በበኩላቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልፀው የህዝቡን ችግር ልባዊ በማድረግ ይህነን የአገልግሎት መስጫ ማዕከል ላስገነባው መንግስት ምስጋናቸውን አቅርበው የላብራቶሪ አገልግሎት መስጫም እንድሰራላቸው ጠይቀዋል።