ከ400 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ህገወጥ መድኃኒቶችን መያዝ መቻሉን የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ገለፀ::

መድኃኒቶች ልያዙ የቻሉት የክልሉ ጤና ቢሮ፣በሸካ ዞን ጤና መምሪያና በየኪ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት እንዲሁም በተቀናጀ ግብረኃይል መሆኑ ተገልጿል።
ህገወጥ መድኃኒቶችና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች የተገኘባቸው የጤና ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱም ተገልጿል።
በክልሉ ጤና ቢሮ ጤናና ጤና ነክ ግብዓት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን የጤናና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር የባለሙያዎች ፈቃድ ዳይረክቶሬት አቶ አብዱልአዚዝ ፈረጃ በወቅቱ እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት ጤና ቢሮ የወባ ወረርሽኝ ቁጥጥር ግብረኃይል አቋቁሞ ስርጭቱን ለመግታት ሰፊ ርብርብ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
አቶ አብዱልአዚዝ አያይዘውም የተቋቋመው ግብረኃይል ከሸካ ዞንና በየደረጃው ከሚገኙ አካላት ጋር በመሆን በዞኑ የኪ ወረዳና ቴፒ ከተማ ባደረገው ቁጥጥር በኢትዮጵያ ምግብ መድኃኒት ባለስልጣን ያልተመዘገበና ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠ መድኃኒት እንዲሁም በግል ጤና ተቋማት የማይያዙ የወባ መድኃኒቶችን መያዝ መቻሉን ጠቁመዋል።
በመደበኛ የሚመጡና በመንግስት ጤና ተቋማት ብቻ መገኘት ያለባቸው ነገር ግን ከመንግስት ጤና ተቋማት በስርቆት ወጥቶ በግል ጤና ተቋማት የተገኙ መድኃኒቶችን ግብረኃይሉ ባደረገው ቁጥጥር መያዝ መቻሉን በክልሉ ጤና ቢሮ የምግብ መድኃኒት ዳይረክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግም ከበደ ገልፀዋል።
ወ/ሮ ዳግም ከበደ አያይዘውም ከደረጃ በላይ በመጀመሪያ ደረጃ ክሊኒኮች ልገኙ የማይገባቸው የፅንስ ማቋረጫ ቁሳቁሶችና ህጋዊ ደረሰኝ የሌላቸው መድኃኒቶች መያዛቸውን ተናግረዋል።
እየተንሰራፋ የመጣውን የወባ ስርጭት መነሻ በማድረግ ህገወጥ ተግባራት በመበራከቱ ህብረተሰቡ የቁጥጥር ባለቤት እንዲሆን የጠየቁት ወ/ሮ ዳግም ከበደ መሠል ድርጊቶችን ስያዩ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ጥቆማ እንዲያደርስ ሲሉም በአፅንኦት አሳስበዋል።
በሸካ ዞን ጤና መምሪያ የጤናና ጤና ነክ ግብዓት አገልግሎት ጥራት ቁጥጥር ዳይረክቶሬት አቶ ኃይሌ ኃይሌ አረንጎ በበኩላቸው በዞኑ እየተንሰራፋ የመጣውን የወባ ስርጭት ለመከላከልና መቆጣጠር እየተደረገ ያለውን በምያደናቅፉ የግል ጤና ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል።
አቶ ኃይሌ አያይዘውም የተጀመረው የተቀናጀ ቁጥጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለው ህብረተሰቡም የጀመረውን የማጋለጥ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በተደረገው ክትትል ከ400 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች እና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች መያዛቸውን የገለፁት አቶ ኃይሌ በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ህገወጥ መድኃኒት ክትትልና ቁጥጥር ላይ የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ሲል የዘገበዉ የሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነዉ።