የሆስፒታሉን አገልግሎት አሠጣጥ ለማሻሻል ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

የኦዳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን የ2017 ዓ.ም 1ኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ላይ ከቦርድ አባላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የሆስፒታሉን የ1ኛ ሩብ ዓመት ሪፖርት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰላሙ ገዳዎ አቅርበው ውይይት ተደርጓል ።
የሆስፒታሉ ጤና ባለሙያዎችን እና የአስተዳደር ሰራተኞችን በማስተባበር በወር ከ10 ብር እስከ 50 ብር ከደመወዝ በማዋጣት የደሃ ደሃ ዜጎች አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ መሠራቱን ስራ አስክያጁ ገልጸዋል።
የህክምና መሳሪያ ጉድለት፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት፣ የመድኃኒት ማከማቻ ስቶር አለመኖር፣ የሰው ሀይል አለመሟላት፣ የአጠቃላይ ኦፕሬሽን ስራ አለመጀመር እና የማዐጤመ ቅድመ ክፍያ የሆስፒታሉን አገልግሎት ያማከለ አለመሆኑ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተግዳሮት እንደሆነም ስራ አስኪያጁ አመላክቷል።
የባለሙያ እጥረት ያሉባቸው ቦታዎች ላይ የማሟላት ስራ ጊዜ ሳይሰጥ መሠራት እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰጡ የቦርዱ አባላት ተናግረዋል።
የወባ ጫናን ለመቀነስና የሴቶች ልማት ህብረት ለማጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡም የቦርዱ አባላት በአስተያየታቸው ጠቁመዋል።
የባለሙያ እጥረት ባሉባቸው መደቦች ላይ አቅም በሚፈቅደው መልኩ ባለሙያ ለማሟላት ወረዳው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የጠሎ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አስናቀ አዋጎ አስረድተዋል።
ከነዳጅ እና ሌሎች የግብዓት እጥረት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመቅረፍ ለማህበረሰቡ በማቅረብ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ማስቀጠል እንደሚገባ አቶ አስናቀ ገልጸዋል።
የእናቶችና ህፃናት ሞትን ለመቀነስ በሆስፒታሉ የተጀመረው ሥራ በቀጣይ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ እና የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ ተናግረዋል።
የሆስፒታሉን አገልግሎት አሠጣጥ ለማሻሻል ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው የገለጹት የቦርዱ ሰብሳቢ የማህበረሰብ ተሳትፎንም ማጠናከር እንደምገባ አሳስቧል።
በሆስፒታል ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት መጣር እንደሚያስፈልግም አቶ ደመላሽ ተናግረዋል።
የመድኃኒት እጥረትን ለመቅረፍ የፋይናንስ ተቋማት ለግዢ የተያዘውን ገንዘብ በወቅቱ መስጠት እንዳለባቸው በመግለጽ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሞዴል ፋርማሲ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመጨረሻም የሆስፒታሉ ባለሙያዎች እና የአስተዳደር ሰራተኞች አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ላደረጉት መልካም ተግባር አቶ ደመላሽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘገባው የጠሎ ዘረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።