የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት የ2016 በጀት ዓመት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የምርመራና ልየታ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፣
የሚዛን አማን ጤና ጽህፈት ቤት የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት “አብሮነትና በጎነት ለኢትዮጲያ ከፍታ“በሚል መሪ ቃል የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ከባለ-ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወነ መሆኑም ተገልጿል።
አገልግሎቱን ያስጀመሩት የከተማ አስተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ታቻ የክረምት ወራት በጎ ፈቃድ ተግባር ለማህበረሰቡ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸው በዛሬው እለት የተጀመረው የግፊት፣ የስኳር ምርመራና ህክምና አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አብራርተዋል።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ወንድሙ አይሳ በበኩላቸው በክረምት በጎ ፈቃድ ደም ልገሳ የበጎ ፈቃድ የደም ልገሳ አገልግሎት የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ 100 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሃላፊው አክለውም ለ182 የማህበረሰብ ክፍሎችን የደም ግፊት ምርመራ አገልግሎት ለመስጠት ከዞንና ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመቀናጀት ማስጀመር መቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህ ስራ ጎን ለጎን የኤች-አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ለ9,000 ህዝብ መስጠትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ምርመራ የተግባሩ አካል መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል።
የማህጸን በር ካንሰር ልየታና ምርመራ፣ የመንገደኛ ሽንት ቤቶችን መገንባት፣ ለእናቶች ማቆያ የሚሆን ፍራሽ፣ ብርድ ልብስና አንሶላ ማሰባሰብና ማሰራጨት፣ ሁሉንም የእናቶች ማቆያ ምቹና ተስማሚ ማድረግ፣ የአካባቢ ጽዳትና ውበት መጠበቅ ወባን በሽታን መከላከል በትኩረት ከሚሰራባቸው የበጎፈቃድ ዘርፎች መሆናቸው ተጠቅሷል።
ዘገባው የሚዛን ከተማ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።