የማህፀን በር ካንሰር በሽታ በሴቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የሚሰጠዉን ክትባት መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት ማስጀመሪያ መርሀግብር በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በአዘነ ውቤ መታሰቢያ አካዳሚ ተካሂዷል።
የማህፀን በር ካንሰር በሴቶች ላይ እያመጣ ያለዉን ጉዳት ለመቀነስና ለመቆጣጠር ክትባቱ ከ9 ዓመት እስከ 14 ዓመት ላሉ ሴት ልጆች ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 7 ቀናት በየጤና ተቋማት እና በትምህርት ቤቶች እንደሚሰጥ በሸካ ዞን ጤና መምሪያ የእናቶችና ህጻናት ዳይረክቶሬት ቡድን መሪ አቶ አስታወሰኝ አደሎ ተናግረዋል።
የበሽታዉን ሥርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሁሉም የጤና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተዉ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል አቶ አስታወሰኝ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይረክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር እንዳለ ሳህሌ የማህጸን በር ካንሰር በሀገራችን በካንሰር ምክንያት ለህልፈት ከሚዳረጉት እናቶች መካከል የማህጸን በር ካንሰር 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝና በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስና ገዳይ ቫይረስ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ቫይረሱን ለመከላከል ከ9 እስከ 14 የዕድሜ ክልል ዉስጥ ለሚገኙ ሴት ልጆች እንደ ክልል ከ1 መቶ 57 ሺህ በላይ ለሚሆኑት እንደሚሰጥና ከዝህም 7ሺህ 8 መቶ ያህሉ በሸካ ዞን እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ቫይረሱን ለመከላከል ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ሴት ልጆች ከግብረ ሥጋ ግንኙነት መታቀብ እንዳለባቸዉ የመከሩት ዶክተር እንዳለ ዕድሜያቸዉ ከ30 ዓመት በላይ ያሉ ሴቶች ቀድሞ ምርመራ በማድረግ ቫይረሱን መከላከልና መቆጣጠር እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።
ክትባቱ ፍቱን መድኃኒት መሆኑና የጎንዮሽ ጉዳት የለሌዉ መሆኑ በሳይንስ የተረጋገጠ በመሆኑ ህብረተሰቡም ከ9 እስከ 14 ዕድሜ ያሉ ሴት ልጆቻቸዉን እንዲያስከትቡ አሳስበዋል።
ዘገባው የሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።