የቅድመ መከላከል ስራዎችን በሁሉም መዋቅሮች ተግባራዊ በማድረግ በወባ በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ላይ እመርታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ ተገለጸ።
የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ “የወባ በሽታን መከላከል ከእኔ ይጀምራል” በሚል መሪ ቃል ዞናዊ የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር የንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን ተካሂዷል።
የቤንች ሸኮ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ደግፌ ኩድን በመድረኩ ማጠቃለያ እንደተናገሩት ወባን ጨምሮ አጠቃላይ የጤና ልማት ስራችን በሳይንሳዊ ትንታኔና በተቀናጀ መልኩ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ጤናው የተጠበቀና የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር የቅድመ መከላከል ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የወባ በሽታ በህብረተሰቡ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ክፉኛ ከመጉዳቱ ባሻገር ክቡር የሰው ህይወትን እየቀጠፈ በመሆኑ በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
ከክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በኀላ የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎቱ እየሰጠ ያለውን ፋይዳ መፈተሽ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ደግፌ በሆስፒታል ፣ ጤና ጣቢያ የባለሙያውዎች ሙያዊ ስነ ምግባር ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና ምክትል የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ቦጋለ እንደተናገሩት በጤናው ዘርፍ ሙያዊ ስነ ምግባር ከምንም በላይ ትኩረት የሚሰጠው ነው ብለዋል። የጥቂቶች የስነ ምግባር ጉድለት የብዙሀኑን ባለሙያዎች ገጽታ እያበላሸ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያ የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር መገለጫ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል አመራሩ ወረድ ብሎ ሊሰራና ተቋማቱን ሊፈትሽ ይገባል ብለዋል።
የቅድመ መከላከል ስራው የምንግዜም ተቀዳሚ ተግባር ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ያሉት አቶ ታምራት በቀጣይ በወባ በሽታ ላይ እመርታ ማስመዝገብ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል። የወባ በሽታ ወረርሽኝ ጫናን ተከትሎ የምግብ እጥረትና የኩፍኝ በሽታ ወረርሽን ሊከሰት ስለሚችል የቅድመ ጥንቃቄ ስራ አብሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ምናሴ እንደተናገሩት ህብረተሰቡ ዘንድ ወባ በላብ ይተላለፋል ፣ አሁን ፀሀይ ነው ወባ የለም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳለ ገልጸው አመራሩና ባለሙያዎች የግንዛቤ ስራ ላይ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። የመከላከል ተግባሩ በመዋቅሮች ወጥነት የሌለው መሆኑ ፣ የጤና ኤክስቴንሽን ስራው ደካማ መሆን አሁንም ተግዳሮት ነው ብለዋል።
አቶ ኤሊያስ አክለውም እንደ ዞን አሁን ላይ ምንም አይነት የወባ በሽታ መድሀኒት እጥረት እንደሌለ ገልጸው ህብረተሰቡ ቅድመ መከላከልን ተግባራዊ እያደረገ ህመም ሲኖር በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አገልግሎት ማግኘት ይችላል ብለዋል።
ምክር ቤቶች ደንቦችን በማውጣት ህብረተሰቡን በዘመቻ አካባቢውን እንዲያፀዳ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ንቅናቄውን አስመልክቶ በመምሪያ የመወያያ ሰነድ የቀረበ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊዎች ሰነዱንና ዞናዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን መነሻ በማድረግ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ተሳታፊዎቹ እንደተናገሩት የጤና ጉዳይ መሰረታዊ መሆኑን ጠቁመው ባለፉት አመታት እንደ ዞን የነበረው የወባ በሽታ ወረርሽን ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል ብለዋል።
በአንዳንድ ወረዳዎች የኬሚካል ርጭት ፣ የአጎበር ዕደላና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመከላከል ስራ በመሰራቱ የወረርሽኑ ጫና እየቀነሰ መሆኑን ገልጸዋል።የሆስፒታል ፣ ጤና ጣቢያና ጤና ኬላዎች የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ጉድለት ፣ የጤና ኤክስቴንሺን አገልግሎት መቀዛቀዝ በስፋት ይታያል ብለዋል።
በመድረኩ የወረዳ አስተዳዳሪዎችና የፓርቲ ኃላፊዎች ፣ የምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች ፣ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በዕለቱ የክልሉ ጤና ቢሮ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዞኑ የማህፀን ጫፍ ካንሰር ክትባት በሚዛን ቁጥር 1 ትምህርት ቤት የማስጀመር ስራ ተሰርቷል።
ዘገባው የቤንች ሸኮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው