የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት የወባ በሽታ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጣር ንቅናቄ መድረክ አደረገ
የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት የወባ በሽታ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጣር ንቅናቄ መድረክ አደርጓል።
የንቅናቄ መድረኩን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አስማማው አደመ የንቅናቄ መድረክ ዳግም የተፈለገው የተጀመሩ የወባ ወረርሽኝ መከላከል ስራዎች እየተዘነጉ በመምጣታቸውና በሽታውም እያገረሸ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ወባ ገዳይ መሆኑን ሁሉም በመገንዘብ ህይወት ለማዳን መሰላቸት አያስፈልግም ያሉት አቶ አስማማው ቀደም በተጀመረው የመከላከል ዘመቻ ስራ ውጤት በመኖሩ ስለወረርሽኙ ለህዝብ ትክክለኛ ግንዛቤ በመስጠት ክፍተቶችን በመለየት በቅንጅት መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደር ሸታ ፣ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ቀጠናዎች ትኩረት የሚሹ ናቸው ያሉት አቶ አስማማው ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን በመለየት ከተለመደው አሰራር ወጥተው ችግር ፈቺ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የዘመቻ ስራ በፓርቲ የሚመራና ክትትል የሚደረግ መሆኑን የተናገሩት አቶ አስማማው በንቅናቄው የባለድርሻ አካላት እንዲሳተፍ የተደረገው አመራሩና ባለሙያው ተቀናጅተው በሁሉም ቀጠና ህዝበዊ ንቅናቄ በማድረግ ውጤታማ ስራ በመስራት የማህበረሰቡን ህይወት መታደግ እንዲቻል መሆኑን አክለዋል።
የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለሙ ብርሃኑ መወያያ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጓል።
የወባ በሽታ በዓይን በማይታይ ፕላስሞዲዬሞ በሚባል ረቂቅ ተዋህሲያን አማካይነት የሚመጣ እንደሆነ እና የወባ በሽታ ስሜቶችና ምልክቶች ቀላልና ከባድ በመባል በሁለት የሚመደቡ ናቸው ብለዋል።
የወባ የትንኝ ቁጥጥር ፣መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የማህበረሰብ ተሳትፎና ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎችን መሥራት ፣የወባ በሽታ ቅኝት፤ አሰሳ፤ ክትትልና ግምገማን ማጠናከር ፣ምርመራና ህክምና መስጠት የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ዋና ዋና ምሶሶ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የጤና ጉዳይ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ ሳይሆን የሁሉም መሆኑን አስተያየታቸውን ያጋሩት የንቅናቄ መድረክ ተሳታፊዎች በየአካባቢው ያሉት ሆቴሎች የቆሻሻ እና ፈሳሽ አወጋገድ በተገቢው መንገድ እንዲሆን በሚመለከተው አካላት ክትትል መደረግ አለበት ብለዋል።
መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመከላከል የተቋም ዕቅድ አካላት አደርገው መሰራት አለባቸው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች ጨፌ እና ለተለያዩ ልማቶች የተቆፈሩ ትላልቅና የመንግስት እና የሌሎችን ድጋፍ የሚጠይቁ መሆናቸውን አንስተዋል።
የማዘጋጃ ቤትና የጤና ጽ/ቤት ቅንጅታዊ ስራ ለወባ ወረርሽኝ መከላከል ትልቅ ሚና በመኖሩ ማዘጋጃ ቤቱ ትኩረት እንዲሰጥ የጠየቁት ተሳታፊዎች የመድሃኒት ስርጭት በጤና ኤክስቴንሽን እጅ እንዲኖር ቢደረግ ብለዋል።
ከዞኑ በወባ ወረርሽኝ ተጋላጭ ከሆኑ መዋቅሮች አንዱ ቦንጋ መሆኑን የተናገሩት የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አረጋ አመራሩ የህዝብ ተሳትፎ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ፖለቲካውንም ሆነ የትኛውንም ተግባር ውጤታማ ለማድረግ መጀመሪያ የሰው ህይወት ማትረፍ ቀዳሚ ስራ ይሆናል ያሉት አቶ ሀብታሙ የግንዛቤ ስራ ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት ብለዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱት አስተያየትና ሀሳቦች ከመድረኩ ማብራሪያ ተሰጥተው የንቅናቄ መድረክ ተጠናቋል።