የተለያዩ የንፅህና መጠበቅያ ቁሳቁሶችን እያመሰቱ ለገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን በሺሾ እንዴ ወረዳ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ገለጹ።
በሺሾ እንዴ ወረዳ ሳኒቴሽን ማርኬትንግ በስራ ማህበር የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ፣ ሳሙና እና የሽንት ቤት ስላቮችን በማምረት እንደሚገኙም ታውቋል።
የማህበሩ ሰብሳቢ የሆኑት ወጣት ታደለ ወልደሚካኤል ”ማርኬትንግ ቤዝድ ሳኒቴሽን ለውጥ በስራ ማህበር ” በክልሉ ጤና ቢሮ ፣ በወረዳው ኢንተርፕራይዝና፤ ንግድ፤ ስራና ክህሎት ፅ/ቤት እና በፅዱ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ በጋራ ባደረጉት የስልጠና እና የቁሳቁስ ድጋፍ የተለያዩ የንፅህና መጠበቅያ ቁሳቁሶች በማምረት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ማህበሩ በስልጠናው በቀሰሙት ልምድ ዘመናዊ የሽንት ቤት ስላቮችን በተሻለ ዲዛይን በጥራት እያመረቱ ሲሆን ስላቡ ተፈላጊ በመሆኑ በትዕዛዝ አምርተው ለደበኞች እያስረከቡ እንደሆነ ወጣት ታደለ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ማህበሩ ባገኘው ዘመናዊ የልብስ ስፌት ማሺን የሴቶች ንፅህና መጠበቅያ ሞዴስንም እያመረተ መሆኑን ገልጸዉ ሞዴሱ ለአንድ ጊዜ ብቻ ተጠቅመው የሚጥሉት ሳይሆን በውሃና ሳሙና አጥበው ለሁለት ዓመት ያህል መገልገል የሚያስችል ዘመናዊ ሞዴስ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ማህበሩ ፈሳሽ ሳሙናን እያመረተ ለደንበኞች እንደሚያቀርብ ወጣት ታደለ ወልደሚካኤል የገለጸ ሲሆን ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የቀረበውን ሳሙና በመግዛት የራሱንና የአከባቢውን ንፅህና እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
የሺሾ እንዴ ወረዳ ንግድ፥ ኢንተርፕራይዝ፣ ስራና ክህሎት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አሳዬ አበቶ ለወጣቶቹ ቋሚና ጊዜያው ስራ ዕድል ለመፍጠር ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰራ መሆኑን አብራርተው የዕድገት በስራ ማህበር የዚሁ ስራ ውጤት አንዱ አካል መሆኑን ገልፀዋል።
ማህበሩ በንፅህና መጠበቅያ ውጤቶች ላይ ተሰማርተው መገኘታቸው ፅዱ አከባቢን ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሆነ ገልጸዋል።
ማህበሩን ለመደገፍ ፅዱ ኢትዮጵያ የተባለው ኢኒሼቲቭ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የማቴርያል ድጋፍ ማድረጉን አቶ አሳየ ገልጸው የክልሉ ጥና ቢሮና የወረዳው ንግድ፥ ኢንተርፕራይዝ፣ ስራና ክህሎት ጽ/ቤት ሙያዊ ድጋፍ ሰጥተዋል ብለዋል።
ወጣቶቹ የሚያመርቱት ምርት በጥራት ተወዳዳሪና በዋጋ እጅግ ተመጣጣኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ ምርቶቹን እየገዛ የግልና የአከባቢ ንፅህና እንዲጠበቅ ማበረታታት ይገባል ብለዋል።
መረጃው የሺሾ እንዴ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ነው ።