የአለም ጤና ድርጅት የውሃ ጥራት መመርመሪያ ኪቶችን ድጋፍ አደረገ ::
ጤና ሚኒስቴር በውሃ ጥራት መጓደል ምክንያት የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችሉ በፖሊሲ የተደገፉ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ የሆኑት ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት ዛሬ የተበረከቱት ተንቀሳቃሽ የውሃ ጥራት መመርመሪያ መሳሪያዎች የውሃ ብክለትን ቀድመው በመለየት ኮሌራን ጨምሮ የውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ ብለዋል።
የመመርመሪያ ኪቶቹ ለ23 የኮሌራ እና ሌሎች የአደጋ ጊዜ ተጠቂ ወረዳዎችን በመለየት ይሰራጫሉ ያሉት
ዶ/ር ደረጄ ለሁሉም ክልሎች በአማካኝ ከ6.5 እስከ 7 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ናቸው ብለዋል።
የፍተሻ ኪቶች የክልል ጤና ቢሮዎችና የወረዳ ጤና ፅህፈት ቤቶች የውሃ ጥራት ክትትልን ለማድረግ አቅማቸውን እንደሚያሳድግ ተጠቁሟል።
የውሃ ጥራት መመርመሪያ መሳሪያዎች የኮሌራ ወረርሽኝን ጨምሮ በውሃ ጥራት መጓደል ምክንያት የሚከሰቱ የህብረተሰብ ጤና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የተናገሩት የአለም ጤና ድርጅትን በመወከል ዶ/ር ሰናይት ተከስተ ናቸው።
25 የውሃ ጥራት መመርመሪያ መሳሪያዎች 8.7 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ግዢ የተፈጸመ ሲሆን በዛሬው እለት 14 ኪቶችን ማስረከብ ተችሏል ያሉት ዶ/ር ሰናይት የቀሩት 11 ማሽኖች በመጓጓዝ ሂደት ውስጥ ናቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ እናስረክባለን ብለዋል።
ዶ/ር ሰናይት አክለውም እንደዚህ ያሉ የትብብር ስራዎች በአለም ጤና ድርጅት እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት መንፈስ የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል።