የአፍላ ወጣቶችን እርግዝና ለመከላከል እና የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ በአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤና፣የአፍላ ወጣቶችን እርግዝና ለመከላከል በተቋቋመዉ ብልህ ጅምር (RISE) ፕሮግራምና በማህጸን ዉስጥ የሚቀመጥ የረጅም ጊዜ ቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በታርጫ ከተማ ዉይይት አካሂዷል።
በዚህ ዉይይት ተገኝተዉ ዉይይቱን የመሩት የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በአፍላ ወጣትነት እድሜያቸዉ የምወልዱ አፍላ ወጣቶች ከወሊድ ጋር በተገናኘ በምወለዱ ህፃናትም ሆነ በእናት ላይ የሚከሰት የጤና ችግር እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለመከላከል የአፍላ ወጣቶችን እርግዝና ማዘግየት የእናትንም ሆነ የልጁን ጤና መጠበቅ በመሆኑ የክልሉ ህብረተሰብና ለዚህ አላማ የተቋቋመው ክልላዊ ስትሪንግ ኮሚቴ የድርሻቸዉን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀላፊው አክለዉ የብልህ ጅምር(Smart start) ፕሮግራም ከኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ስራ ጋር እንዲቀናጅ አጋር ድርጅቶች ትኩረት ሠጥተዉ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
አቶ ኢብራሂም ክልሉ በአሁኑ ወቅት በርካታ አጋር ድርጅቶች ጋር ለመስራት በሩ ክፍት በመሆኑ በዚህ ዉይይት የተገኙ አጋር ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች ፕሮግራማቸዉን በማስፋትና የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍ የህብረተሰባችንን የአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ዙሪያ፣የኤች አይ ቪ መከላከል እና መቆጣጠር እንዲሁም ሌሎች የጤና ዘርፎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ዉይይት ላይ የተሳተፉ የክልል ጤና ቢሮ ም/ሀላፊና የጤና ፕሮግራሞች ሀላፊ አቶ ሀይሌ ዘዉዴ፣የእናቶችና ህፃናት ጤናና የስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሠረት ወ/ማሪያም፣የበሽታ መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይረክተር ዶ/ር እንዳሌ ሳህሌ፣የክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ልማት ዕቅድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዋሲሁን ብርሃኑ እና የሎጅስትክ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበበ ከበደ በሰጡት አስተያየት የአፍላ ወጣቶችንና ወጣቶችን ጤና መጠበቅ ትዉልድን ማዳን መሆኑን ገልጸዉ የክልላችን አፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን ጤና ለመጠበቅ በሜጋ ፕሮጀክቶችና በትልልቅ ኢንቨስትመንት ሥፍራዎች የሚገኙ አፍላ ወጣቶችና ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የጤና አገልግሎት መሰጠት እንዳለበትና ለዚህም የክልሉ ጤና ቢሮ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚሁ ውይይት እንደተገለጸው በኘሮግራሞቹ ማዕቀፍ የሚሰጡ የስነ- ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ለተጠቃሚው ህ/ሰብ ከማድረስ አንጻር ፊት የወጡ ወረዳዎች እንዳሉ ሁሉ አሁንም ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስራ የሚጠይቁ ወረዳዎች የተለዩ በመሆናቸው በቀጣይ ድጋፍና ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ተገለጿል።
በመንግስትና አጋር ድርጅቶች በጋራ ለህ/ሰቡ የተሰጡ በርካታ የስነ-ተዋልዶ አገልግሎቶች አበረታች ቢሆንም ያከናወኑት ስራዎች መረጃ በክልሉ ጤና ቢሮ የመረጃ ቋት ውስጥ የሚገባበት የአሰራር ስርዓት ውስጥ መግባት እንዳለበት ተገልጿል።
በዉይይቱ ማጠቃለያ ላይ የቢሮ ሀላፊ በአፍላ ወጣቶችና ወጣቶች ጤናና በብልህ ጅምር(Smart Start) በአፈጻጸማቸዉ ወደሁዋላ የቀሩ ዞኖች ላይ የስትሪንግ ኮሚቴ አባላት በባለቤትነት እንዲሰሩና ባለቤት ይኖረዉ ዘንድ የስትሪንግ ኮሚቴ አባላትን አሳስበዉ የእለቱ ዉይይት ተጠናቋል
በዚህ ዉይይት የPSI/E እና የMSIE የሚባሉ አጋር ድርጅቶች ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል