የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኀበር የዳውሮ ታርጫ ቅርጫፍ መድኃኒት መደብር ተመርቆ ለአገልግሎት ጀመረ።

ማኅበረሰቡን በጤና ዘርፍ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት በቅንጅት እያከናወነ ባለው ተግባር ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ እንዳለ የዳዉሮ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የዳዉሮ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከተቋቋመ ከሁለት ዓመታት ወዲህ በናዳ፣ በድርቅ፣ በድንገተኛ አደጋና በሽታ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች የህክምና ቁሳቁስ በማቅረብ፣ አልባሳትና ምግብ በማዘጋጀት እንዲሁም የአምቡላንስ አገልግሎት በመስጠት ሰብዓዊ እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱም ተገልጿል።
በመሆኑም የአገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ለማሳደግ እንዲቻል አሁን ላይ በመድኃኒት አቅርቦትና እጥረት የሚታየውን ችግር ለመፍታት እንዲቻል ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመቀናጀት በታርጫ ከተማ የመድኃኒት መደብር ተከፍቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ማኅበሩ አስችሏል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በድንገተኛ አደጋ ላይ ሰብአዊ እርዳታ የሚሰጥ ተቋም ሲሆን የመንግሥት አጋዥ ድርጀት በመሆን ተግባሩን እየተወጣ እንዳለ የገለጹት በማኅበሩ የዳውሮ ታርጫ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባቴ ጀምበሬ ናቸው።
የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት በጋራ ለማረጋጋጥ እንዲቻል የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በዳውሮ ታርጫ ቅርንጫፍ ጽሕፈት የተርጫ መድኃኒት መደብር ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ማልዳዬ በበኩላቸው ማኅበሩ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ ለአከባቢው መሠረታዊ የሆኑትና ጥራታቸው የተረጋጋጠ መድኃኒቶችን በቅናሸ ዋጋ በማቅረብ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልፀዋል።
መድኃኒቱ ለተጠቃሚዎች ቅናሽ በሆነ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ በመሆኑ የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራም አቶ መንግሥቱ አብራርተዋል።
የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው ማኅበረሰቡን በጤና ዘርፍ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን በመለየት የሚታዩ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ በማናቸውም የልማት ዘርፎች ነዋሪዎችን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየተከናወነ የሚገኘው ተግባር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝም በመጠቆም።
ዛሬ በተካሄደው የመድኃኒት መደብር ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ጨምሮ የዞኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የጤና ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት የመደብሩን አገልግሎት በይፋ አስጀምረዋል።
ዘገባው የዳውሮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።