የክልሉ ጤና ቢሮ ከአለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በዳውሮ ዞን ገና ወረዳ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የአልሚ ምግብ ድጋፍ አደረገ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በዳውሮ ዞን ገና ወረዳ በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውና የማህበረሰብ ክፍሎች የአልሚ ምግብ ድጋፍ አደርጓል።
የአልሚ ምግብ ድጋፍ በገና ወረዳ ተገኝተው ያስረከቡ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ድጋፉ በተገቢው ለተጎጂ የማህበረሰብ ክፍሎች መድረስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በወረዳው በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸውና ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች 48 ሺ ኪሎ ግራም አልሚ ምግብ ተደራሽ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን አልሚ ምግቦቹ ህፃናትን፣ አጥቢና ነፍሰ ጡር እናቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተብራርቷል።
በዳውሮ ዞን ከገና ወረዳ በተጨማሪ በዛባ ጋዞ ወረዳ ለሚገኙ ለ2736 ህፃናትና ለ1185 ነፍሰጡርና አጥቢ እናቶች ከ37 ሺ 655 ኪሎ ግራም የሚሆን የአልሚ ምግብ ድጋፍ ማድረግ መቻሉንም አብራርተዋል።
በዞኑ በሎማ፣ በዲሳና በታርጫ ዙሪያ ወረዳ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችም ድጋፍ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በክልሉ በተመሳሳይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያትጉዳት ለደረሰባቸውና ለሚደርስባቸው በካፋ ዞን ጎባና ጨታ ወረዳዎች እንዲሁም በምዕራብ ኦሞ ዞን ሜኒት ጎልድያና ማጂ ወረዳዎች ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የአልሚ ምግብ ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም አቶ ኢብራሂም አስረድተዋል።
ድጋፉን የተረከቡ የገና ወረዳ ምክትል አስተዳደርና የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቡላዴ ቡልቱሞ የክልሉን ጤና ቢሮንና ሌሎች የባለድርሻ አካላትን አመሰግነው ድጋፉን በአጭር ቀናት ውስጥ ለተጎጂዎች ለማድረስ በሀላፊነት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
በመጨረሻም የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ያመሠገኑ አቶ ኢብራሂም ወቅቱ የወባ በሽታ አስተላልፊ ትንኞች በብዛት የሚራባበት ወቅት ስለሆነ ማህበረሰቡ የወባ በሽታ መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ድጋፉ የመጠባበቂያ ያካተተ መሆኑን አቶ ኢብራሂም ገልጿል።
ዘገባው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ነው::