የክልሉ ጤና ቢሮ ከ6 መቶ ሺ ብር በላይ ወጪ በማውጣት በቦንጋ ከተማ ያሰራውን የሁለት አቅመ ደካሞችን ቤት አስረከበ::
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከ6 መቶ ሺ ብር በላይ ወጪ በማውጣት በቦንጋ ከተማ ያሰራውን የሁለት አቅመ ደካሞችን ቤት ርክክብ አደርጓል።
በርክክቡ የተገኙት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ የክልሉ ጤና ቢሮ ማህበረሰብ ተኮር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ኢንሼቲቭ የሆነውን ተግባር በመቀበል አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን ቤት መስራትና መጠገን ከመደበኛ ስራ ባሻገር ለአደጋና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ አካላትን በመለየት በራሱ በጀት ሰርተው በማስረከቡ ምስጋና አቅርበዋል።
የቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በበኩላቸው የክልሉ ጤና ቢሮ በማህበራዊ ዘርፍ ብልጽግና ከሚያረጋግጡ ተቋማት አንዱ መሆኑን የጤና ቢሮ በመሆኑ ቢሮ የተሰጠውን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ጤናን ማጎልበትና በሽታ መከላከል መሰረታዊ ተልዕኮ መሆኑን በመጠቀስ ከመደበኛ ስራ ጎን ለጎን አቅመ ደካማ የሆኑ አካላትን አቅም በፈቀደው ልክ መረዳት እና ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
በክልሉ ለሶስት አመታት በጤና ቢሮ በካፋ ዞንና ዳውሮ ዞን 7 ቤቶችን ወደ 2 ነ ጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ሰርተው ያስረከቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በርክክብ ወቅት ለአሁን የሚያስፈልጉ የመኝታ ፍራሽ፣ትራስ ፣ኮንፎርት ብርድ ልብስ እና ለምግብ አገልግሎት የሚሆን ዘይትና ዱቄት አበርክተዋል።
በተለያዩ በዓላት የማዕድ ማጋራት ተግባር እያከናወኑ እንደሚገኙና በቀጣይም ከሚመለከተው አካላት ጋር በመነጋገር አቅም በፈቀደው መንገድ በ6ቱም ዞኖች በመንቀሳቀስ እንደሚሰሩ አቶ ኢብራሂም አብራርተዋል።
ድጋፉ የተደረገላቸው አካላት ከዚህን በፊት ቤቱ በማፍሰሱና የሚደግፋቸውን በማጣት ችግር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁን ላይ ቤት ተሰርተው በመሰጠቱ መደሰታቸውን ገልፀው ድጋፉን ያደረጉ ተቋማትን አመስግነዋል።
በርክክቡ የዞንና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው የቦንጋ ከተማ ኮሚኒኬሽን ነው።