“በጎነት ለጤንነት” በሚል መሪ ቃል የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ነፃ የህክምና አገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራም በካፋ ዞን ገብረ ፃዲቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ተካሂዷል።
የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራሙን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም እና የካፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ በይፋ አስጀምሯል።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም እንዳሉት” በጎነት ለጤንነት” በሚል መሪ ቃል ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የነፃ ምርመራና ህክምና አገልግሎት ከነሐሴ 1/2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ነሐሴ 30/2016 ዓ.ም ድረስ እንደምሰጥ ገልጸዋል።
የሚሰጡ አገልግሎቶች የስኳር በሽታ ምርመራና ህክምና ፣የደም ግፍት ምርመራና ህክምና፣የማህፀን በር (ጫፍ) ካንሰር ምርመራና የዓይንና የቆዳ በሽታ ምርመራና ህክምና አገልግሎቶች በነፃ የህክምና አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
በተመሳሳይ የኤች.አይ.ቪ ምርመራና የምክር አገልገሎት፣የወባ በሽታ ምርመራና ህክምና፣የቲቢ በሽታ ምርመራና ህክምና፣የስነ-ምግብ እጥረት ምርመራና ህክምና እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ የጤና አጠባበቅ ትምህርት እንደሚሰጥም ገልጸዋል ።
ይህ በጎ ፍቃድ አገልግሎት በክልላችን ባሉ ሁሉም ሆስፒታሎች ላይ ከዛሬ ቀን ጀምሮ ለ30 ቀናት እንደሚሰጥ የተናገሩት ኃላፊው በዚህም አቅመ ደካሞች ገንዘብ ባለመኖሩ ያልታከሙ ሰዎች በአቅራቢያው ያሉ ሆስፒታሎች በመቅረብ የነፃ የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንድሆኑ ጥሪ አስተላልፏል።
በመጨረሻም የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ደም ልገሳ ያካተተ መሆኑን ገልጸው የክልሉ ጤና ቢሮ በቦንጋ ከተማ ለሁለት አቅመ ደካሞች ከ600 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ ሁለት መኖሪያ ቤት እየገነባ እንደሆነም አቶ ኢብራሂም ተማም ተናግረዋል።
“በጎነት ለጤንነት” በሚል መሪ ቃል የ2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በካፋ ዞን ገብረ ፃዲቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል የተጀመረው የነፃ የህክምና አገልግሎት በካፋ ዞን ባሉ ሁሉም ሆስፒታሎች እና በወረዳ ማዕከል የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ላይ ለአንድ ወር እንደሚሰጥ የካፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ ገልጸዋል።
ይህን የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራን የጤና ባለሙያዎች በቅንነት፣በታታሪነትና በታማኝነት ለአቅመ ደካማ ማህበረተሰብ የነፃ ምርመራና ህክምና አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው አቶ አክሊሉ አሳስቧል።
በአሁኑ ወቅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ማለትም ስኳር በሽታ፣ደም ግፊት ፣ካንሰር እና የልብና የደም ስር በሽታዎች ከፍተኛ የመያዝ ሁኔታ ስላለ ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የተናገሩት ኃላፊው ታማሚዎችና ሌሎች ማህበረሰብ በህክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን በመቀበል የአኗኗር ዘይቤ በማስተካከል ከበሽታ ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸሁ ብለዋል።
ዘገባው ፦የካፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው