የክረምት ወራት መውጣትን ተከትሎ የወባ ወረርሽኝ ጫና እንዳያሻቅብ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ በአመራር የተመራ የጤና ባለሙያዎች ቲም ተዋቅሮ ስምሪት መሰጠቱ ተገለጸ።

በወባ ወረርሽኝ መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ለተከታታይ አምስት ወራት የተሰሩ ስራዎች ግምገማ የክልሉ ጤና ቢሮ አመራሮች ዳይሬክተሮች ፣ እና ባለሙያዎች በተገኙበት በታርጫ ከተማ ተገምግሟል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራህም ተማም ባለፉት አምስት ወራት በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራ የደረሰበት ደረጃን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ ምልከታ እንዳደረጉ ገልጸዋል።
የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል የተዘረጋው የአሰራር ስርዓት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገምግመው አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ካለው የበሽታው ስርጭት ጫና አኳያ የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት መጠቆማቸውን አቶ ኢብራሂም ገልጸዋል።
ባለፉት አምስት ወራት በጋራ ርብርብ የተሰሩ ስራዎች ላይ በጉድለት የተለዩት አፈጻጸሞች ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ገልጸው ይህንን ለማጠናከር በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ የክልሉ ጤና ቢሮ ባለሙያዎች ቲም ተዋቅሮ ስምሪት መሰጠቱን ገልጸዋል።
ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ ቲም የወባ በሽታ መተላለፊያና መከላከያ ዘዴዎች ላይ ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል የገጽ ለገጽ እና የተለያዩ ሚዲያዘዎችን ተጠቅሞ የተግባቦት ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመው ሀላፊነት ባለው አካል ያልተረጋገጠ መረጃ በየትኛውም ሚዲያ ማሰራጨት ተጠያቂ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የወባ በሽታ ተዋሲ መዲሀኒት ተላምዳል የሚል ያልተረጋገጠ መረጃዎች በህብረተሰቡ ውስጥ እንደሚዘዋወር ገልጸው ይህ መረጃ ሀሰት እና አሁን በህጋዊ መንገድ የገቡ እና በስራ ላይ ያሉ የወባ ማከሚያ መድሀኒቶችን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ፈዋሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለወባ በሽታ ህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የህዝብ ንቅናቄ በማጠናከር መሰረታዊ የመከላከል ዘዴዎች ላይ ህ/ሰቡ በትኩረት እንዲሰራ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ወረርሽኙን ለመከላከል ሲባል ወደ ወረዳዎች የተላኩ የወባ መከላከያ እና ማከሚያ ግብዓቶች ጥቅም ላይ ያልዋሉ ካሉ በመለየት ስራ እንዲውሉ የማድረግ ስራ መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።
ከጤና ኬላዎች ጀምሮ ባለው የጤና ተቋማት የወባ በሽታ ምርመራ እና ህክምና አገልግሎት በተጠናከረ ሁኔታ መሰጠት እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን የግብዓት እጥረት በጤና ኬላዎች እንዳይፈጠር ድጋፍ ሊደረግ እንደማገባ ተገልጿል።
የመረጃ አደረጃጃትና አላላክ ላይ የተሰሩ አበረታች ስራዎች ያሉ ቢሆንም ጥራት የማምጣት ስራ የአንድ ሰሞን ተግባር ብቻ ሳይሆን የተጀመሩ ጥሩ ስራዎችን በማጠናከር የመረጃ ተዓማኒነቱን የዘውትር ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ተወያይተውበታል።
ለወባ እና ለሌሎችም የጤና አገልግሎት ስራዎች ለጤና ተቋማት የሚላኩ ግብዓቶች በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል መደረግ እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን በተለይ ህገ-ወጥ የመዲሀኒት ቁጥጥር ስራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ መሰራት አለበት ተብሏል።
ከወባ ወረርሽኝ ዘመቻ ጎን ለጎን በመደመኛ የስራ በዕቅድ የሚተገበሩ የጤና ተግባራት በተቀመጠው መርሀ-ግብር መሰረት መፈጸም እንዳለባቸውም የተወያዩበት ሲሆን የሆስፒታሎችን ተግባራት ለማጠናከር የቦርድ ውይይት እና የህዝብ መድረክ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ድጋፋዊ ክትትል ቲሙ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በግምገማ መድረኩ የአምስት ወራት የወባ መከላከል ስራ ሪፖርት እና የመስክ ስራ ስምሪት ቼክ-ሊስት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።