የወባ መከላከልና የክትባት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የካፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አሰፋ አሳሰቡ፡፡

ካፋ ዞን ከሰኔ 17/2016 ዓ/ም ጀምሮ በወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትና የተመዘገቡ ዉጤቶችን በተመለከተ ወደ ወረዳዎች ለድጋፍ ከተሰማሩ ባለሙያዎች፣ከወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ በማህበረሰቡ ውስጥ እየተስፋፋ የሚገኘውን የወባ ወረርሽኝ ለመቀነስ ዓላማ ያደረገ የዘመቻ ተግባር በዞን ደረጃ ንቅናቄ ከተጀመረ 2 ወር ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውንና መሠረታዊ ለውጥ ማምጣታቸውን አንስተዋል፡፡
እንደ ዞን በተሰራው ከፍተኛ የንቅናቄ ስራ የወባ ጫና ሰኔ ወር ከነበረው በሐምሌ ወር በ 29% መቀነስ የተቻለ ቢሆንም አሁንም የተፈለገውን ግብ ለማሳካት የመከላከል ሥራ አጠናክሮ በመስራት የወባ በሽታ በማህበረሰባችን ላይ የሚያሳድረውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡
በመከላከል ተግባር ማህበረሰቡን ማሳተፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት አመላካች መሆኑን ከአንዳንድ ወረዳዎች ተሞክሮ መውሰድ ይገባል ያሉት አቶ አክሊሉ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶችን በየቀኑ በመገምገምና ክፍተቶችን በማረም ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ አሁናዊ የወባ ስርጭት ሁኔታና የተሰሩ የመከላከል ተግባራት እንዲሁም የክትባት አገልግሎት አፈፃፀም ያካተቱ ሰነዶች ቀርቦ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
የመድሃኒት አጠቃቀምና ቁጥጥርን በተመለከተ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ክትትል ማድረግ እንዳለባቸውና የተጠያቂነት አሰራር መስፈን እንዳለበት ተመላክቷል፡፡
እንደዚሁም የመረጃ ጥራትና ተደራሽነት እንደዚሁም ተዓማኒነት ላይ ተገቢ ትኩረት መሰጠት አለበት ተብሏል፡፡
የክትባት ዘመቻን በማጠናከር ውጤታማ ማድረግ ላይ ሁሉም አቋም ወስዶ በቆጠራ የተገኙ ሁሉም ህፃናት በአንድ ሳምንት ውስጥ መከተብ እንዳለባቸውና ህፃናት ባለመከተባቸው ምክንያት ሊከሰት ከሚችል ወረርሽኝ ህፃናትን መታደግ እንደሚገባ ሁሉም ኃላፊነት መውሰድ አለበት ብለዋል፡፡
ለ2017 ዓ/ም ክትባት*የሚወስዱ ህፃናትን ለይቶ የሚያስፈልግ ግብዓት ማቀድ፤የእናቶች ጤና፤የምግብ እጥረት ልየታና ሌሎች ተግባራትን አቀናጅቶ መስራት እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
ወቅቱ የዝናብ ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ ከሚችሉ ድንገተኛ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ማህበረሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ተብሏል፡፡
የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትን በተመለከተ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በወረዳ ማዕከል አገልግሎቱን ፈጥኖ ማስጀመር እንዳለባቸው የጋራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
በመጨረሻም የጤና መምሪያ ኃላፊው የስራ መመሪያ ከሰጡ በኋላ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ የመረጃ ፍሰትን ለማጠናከር ከወረዳ ጤና/ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር የመግባቢያ ውል ሰነድ ተፈራርመው የግምገማና የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡
የካፋ ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነው ።