የወባ ስርጭትን ለመከላከልና መቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግል ጤና ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተጠቆመ
ወቅታዊ የወባ ስርጭትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ በየኪ ወረዳና ቴፒ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ የግል ጤና ተቋማት ባለቤቶች ጋር በቴፒ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የሸካ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ በላቸው ጋራ በወቅቱ እንደተናገሩት የወባ ስርጭትን ለመከላከልና መቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የግል ጤና ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በተከሰተው የወባ በሽታ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ለከፍተኛ ስቃይና እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ በላቸው የግል ጤና ተቋማት ምንም እንኳን ለትርፍ የተቋቋሙ ቢሆንም ወቅታዊ የወባ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ማገዝና ህብረተሰቡን በበጎነት ማገልገል ላይ ትኩረት ልያደርጉ ይገባል ብለዋል።
የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ካይቶ እንደተናገሩት የግል ጤና ተቋማት ሙያዊ ስነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመው አገር ውስጥ ያልተመዘገቡ መድኃኒቶችን፣ለደረጃቸው ያልተፈቀዱ መድኃኒቶችን ከመያዝ ጀምሮ እና ከተፈቀደው ዶዝ በላይና በታች መድኃኒቶችን ለህብረተሰቡ የመስጠት አዝማሚያዎች በስፋት በግል ጤና ተቋማት እየተስተዋለ መሆኑን ገልፀዋል።
አቶ ተሾመ አያይዘውም የግል ጤና ተቋማት አካባቢ የሚስተዋሉ እና ያለባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ዞኑ አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል ብለው ነገር ግን ህግ ከማስከበር ጋር ተያይዞ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ የግል ጤና ተቋማት ባለቤቶች በበኩላቸው ሙያዊ ስነ ምግባርን ተላብሶ አገልግሎት መስጠት ግዴታ መሆኑን የሚስተዋልባቸውን ክፍተት ለማረም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተከሰተውን የወባ በሽታ ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው ወጥ የሆነ አሠራር ልቀመጥ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።
የግል ጤና ተቋማት ባለቤቶች አያይዘውም ያለባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግር ያነሱ ሲሆን ከክልል የመጣው መመሪያ ማለትም የግል ጤና ተቋማት 200 ሜትር ያህል ከመንግስት ጤና ተቋማት መራቅ አለባቸው የተባለው ጉዳይ ለከፍተኛ ስጋት እንደዳረጋቸው በስፋት አንስተዋል።
በመመሪያው መተግበር ላይ ልዩነት የለንም ያሉት የግል ጤና ተቋማት ባለቤቶች ነገር ግን በተለይ እንደ ቴፒ ከተማ ነባራዊ ሁኔታ ለጤና ተቋማት የሚሆን ህንፃ ለኪራይ ማግኘት አልቻልንም ሲሉ በአፅንኦት ገልፀዋል።
እንደ ቴፒ ከተማ ነባራዊ ሁኔታ ብዛት ያላቸው የግል ጤና ተቋማት በ200 ሜትር ውስጥ መሆናቸውን የጠቆሙት ባለቤቶቹ ቢያንስ በከተማው የተጀመሩ ግንባታዎች ተጠናቀው ተከራይተን እስከሚንወጣ ጊዜ ልሠጠን ይገባል በማለት በአፅንኦት ተማፅነዋል።
የዞኑ የግል ጤና ተቋማት ማህበር ሰብሳቢ አቶ መልካሙ ማሞ እንደገለጹት የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት በጤና መምሪያ በኩል ወጥ የሆነ አሠራር ከተቀመጠ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተቋማት አካባቢ የሚስተዋለውን የአሠራር ክፍተት ለማረም ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው ተቋማቱ ያለባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚመለከተው አካል እንዲፈታላቸውም ጠይቀዋል አቶ መልካሙ።
የውይይት መድረኩን መድረኩን የሸካ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ በላቸው ጋራ፣የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ካይቶ እና የዞኑ የግል ጤና ተቋማት ማህበር ሰብሳቢ አቶ መልካሙ ማሞ በጋራ በመሆን የመሩት በቴፒ ከተማና የኪ ወረዳ አስተዳደር የሚገኙ የግል ጤና ተቋማት ባለቤቶች እንዲሁም የዞን፣የየኪ ወረዳና ቴፒ ከተማ አስተዳር ጤና ተቋማት አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን እንደዘገበው።