የወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመታደግ የጤና ተቋም አመራሮችና ባለሙያዎች በትኩረት መሰራት እንደሚጠበቅ ተገለጸ።

በወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የተሰሩ ሥራዎች የእስካሁን አፈፃፀም የክልሉ ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና ለክልሉ ጤና ቢሮ ማኔጅመንት አባላት በታርጫ ከተማ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ክቡር አቶ ወንድሙ ኩርታ የውይይት መድረኩን በመሩበት ወቅት እንደገለጹት ከህ/ቡን የወባ ወረርሽኝ ጫና ለመታደግ ሁሉም አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች ከምን ጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በተለይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በተመደቡበት ጤና ኬላዎች የሚጠበቅባቸውን የስራ ጊዜ በማሳለፍ በተሰጣቸው ሀላፊነት ልክ ተግባራቸውን ማከናወን የማይችሉ ከሆነ ቀጣይነት ያለ ለውጥ ማስመዘገብ አይቻልም ብለዋል።
በተጨማሪም ከጤና ኬላዎች ጀምሮ በተዋረድ የሚገኙ የጤና አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የመገልገያ ቁሳቁሶች እና መዲሀኒቶችን አቅርቦት በማሟላት ተገልጋዩች ሳይቸገሩ መታከም የሚችሉበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበትም ገልጸዋል።
ዋና አፈ- ጉባኤ ክቡር አቶ ወንድሙ ኩርታ በክልሉ ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የሚመራ 4 ቡድን በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከል የተሰራውን ስራ ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ዞን እንደሚወርዱ ገለው የዞኖችን የመከላከል ስራ አፈጻጸም በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጡ ገልጸዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ ተወካይና የህክምና አገልጎሎቶች ዘርፍ ሃላፊ አቶ ምትኩ ታመነ እንደገለጹት የወባ በሽታ በክልሉ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ ከፍ ካለበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ጤና ቢሮ በርካታ ተግባራትን ማከናወን ቢችልም በአንዳንድ ዞኖች የበሽታውን ክስተት በቋሚነት የመቀነስ ሁኔታ እየታዬ አይደለም።
የክልሉ ጤና ቢሮ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የህክምና ቁሳቁሶች እና መድሃኒቶችን ባለማቋረጥ ለታችኛው ጤና መዋቅር ከማቅረቡም በተጨማሪ የጤና ኤክስቴንሽ ባለሙያዎች ተገቢውን አገልግሎት ለህብረተሰቡ እንዲሰጡ የሚያስችል ስልጠናዎችን በተከታታይ መስጠቱንም አስታውሰዋል ።
ከተደረገላቸው ድጋፍ እና ከተሰጠው ስልጠና ልክ በወረዳና እና በቀበሌ ጤና ኬላዎች አካባቢ ለተከሰተው የወባ ወረርሽኝ የመከላከል ስራ በቂ ምላሽ ስላልተሰጠው ለወባ ወረርሽኝ ዘመቻ ስኬት እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።
አሁን ያለንበትና ቀጣይ ወራቶች የክረምት ወቅት መውጫ ስለሆኑ በህ/ሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ አስቀድሞ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮችና የጤና ባለሙያዎ ለጤና ስራ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባል ብለዋል አቶ ምትኩ ታመነ።
ለቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢውች እና ለክልሉ ጤና ቢሮ ማኔጅመንት አባላት በቀረበው ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው በወረዳና በቀበሌ የሚገኙ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ከቃላት ባለፈ በተግባር ስራ ላይ ቁርጠኝነት የማይታያቸው፣ ለመከላከል የተላኩ መድሀኒቶች እና የመገልገያ ቁሳቁስ ክትትል እና ቁጥጥር በተገቢው የማያደርጉ፣ የስነ-ምግባር ችግር በሚስተዋልባቸው ባለሙያዎች ላይ እርምጃ የማይወስዱ ፣ ቀጣይነት ያለው የመከላከል ስራ የማይሰሩ መሆናቸው ተጠቅሷል።
በቀረበው ሪፖር ት መነሻ አንዳንድ ተሳታፊዎች እንደገለጹት አሁንም የህ/ቡን ህይወት ለማትረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከሌሎች ስራዎች ይልቅ ለወባ ወረርሽኝ ዘመቻ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም ህ/ሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ስራ ትኩረት በመስጠት ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ ፣ የማዳፈን እና ህ/ሰቡ የግል እና የአካባቢ ንጽህና እንዲጠበቅ ግንዛቤ ስራ ተሰርቶ በሽታውን የመቀልበስ ስራ እውን መሆን አለበት ብለዋል።