የወባ ወረርሽኙን ለመከላከል አስፈላጊ የህክምና ግብዓት ሊሟሉ ይገባል

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል አስስፈላጊ የህክምና ግብዓት ሊሟሉ እንደሚገባ አሳስቧል።
ቋሚ ኮሚቴው ወረርሽኙን አስመልክቶ በክልሉ ከፋና ዳውሮ ዞኞች እስከ ቀበሌ ድረስ በሚገኙ ጤና ተቋማት የመስክ ምልከታ በማድረግ በህዝቡ ላይ ያደረሰውን የጤና ጉዳት ተመልክቷል።
የቋሚ ኮሚቴው አባልና የቡድኑ አስተባባሪ የተከበሩ ወ/ሮ አሚራ አህመድ በክልሉ የወባ ወረርሽኙን ለመከላከል የተደረገው ጥረት የተሻለ መሆኑን ገልጸው፤ አሁንም ከችግሩ አሳሳቢነት አኳያ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች እና መድሀኒቶች ስርጭት ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ወረርሽኙ ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ህዝብን ያሳተፈ የቅንጅ ስራው ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ያሉት የተከበሩ ወ/ሮ አሚራ የአጎበር ስርጭቱ፣ የኬሚካል የመርጨት እና ያቆሩ ውሃማ አካባቢዎችን የማፋሰስና የማደፈን ስራዎች ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በክልሉ የወባ ጫናው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ወረርሽኙ በሚያይልባቸው 6 ዞኖች ጉዳት ከማድረሱ በፊት የከሚካል አቅርቦት ችግር በአስቸካኳይ እንዲፈታ ለቋሚ ኮሚቴው ተናግረዋል።
ክልሉ በወባ ወረርሽኝ ተጠቂነት የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዝ እንደሆነ ታውቆ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጭምር ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስተባር ይገባልም ብልዋል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች፣ ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋፂዮን ተረፈ ባለፋት ወራት ክልሉ በወባ ጫና ውስጥ በነበረበት ወቅት ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ በተሰራው ስራ ወረርሽኙ መቀነሱን ገልጸዋል።
እንደ ክልል የወረሽኙ ስርጭት አየቀነሰ ቢሆንም፤ ወባማ ተብለው በተለዩ 34 ወረዳዎች ላይ ቀጣይነት ያለው የቅንጅት ስራ የሚጠይቅ ስለመሆኑ ዳይሬክተሩ ሳይገልጹ አላለፉም።
ወረርሽኙ ከፍተኛ ተጽዕኖ ባደረሰባቸው ሀምሌና ነሐሴ ወራት ውስጥ የሰው ሞት የተመዘገበ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋፂዮን፤ አሁን ላይ የስርጭት መጠኑ እንዲቀንስና ሞት እንዲቆም ሁለንተናዊ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ዘገባው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ነው።