የወባ ወረርሽኝን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጤና መዋቅሩ ባለሙያዎችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በቅንጅትና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተጠቆመ
የወባ ወረርሽኝን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጤና መዋቅሩ ባለሙያዎችና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች በቅንጅትና በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተጠቆመ
የክልሉ ጤና ቢሮ ቲም በሸካ ዞን እስካሁን በወባ ወረርሽኝ መከላከልና ቁጥጥር ላይ የተከናወኑ ተግባራትና በቀጣይ ሊሠሩ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቴፒ ከተማ ውይይት አድርጓል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በመድረኩ ተገኝተው እንደገለፁት ከዚህ ቀደም በተቀናጀ መንገድ በተሰራዉ ስራ የወረርሽኙን መጠን መቀነስ ቢቻልም አሁን ባለዉ ሁኔታ የሥርጭት መጠኑ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።ስለሆነም ተከታታይ የሆነ ድጋፍና ግምገማ በማድረግ ርብርብ በማድረግ መግታት ይገባል ብለዋል።
ወረርሽኙን በዘላቂነት ለመከላከል መራቢያ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን እንድሁም የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በተቀናጀ መንገድ ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል።
አክለውም ህብረተሰቡን የማስተባበር ስራ ከሠራን በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀነስ እንችላለን ብለዋል ።
የክልሉ ምክር ቤት ህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አምሳሉ ንጋቱ በበኩላቸው ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየደረጃው የሚገኙ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
ለወባ ወረርሽኝ መስፋፋት አንዱ ምክንያት የአካባቢ ፅዳት ችግር መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ አምሳሉ ንጋቱ በዚህ ላይ የጤና ባለሙያዎች ከዞን እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማወያየትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
አክለውም ወረርሽኙን በዘላቂነት ለመከላከል በየደረጃው ውይይት በማድረግ መራቢያ ቦታዎችን በማፋሰስና በማዳፈን በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ማጠናከር፤ የአጎበር አጠቃቀም ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራት ፤ ወረርሽኙን ለመከላከል የፖለቲካ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሠራ እንደሚገባ፤ የክልሉ ጤና ቢሮ ድጋፍና ክትትል መጠናከር እንዳለበት የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የጤና ጉዳይ ሁሉንም የሚመለከት በመሆኑ ከዞን እስከ ታችኛዉ መዋቅር ድረስ የመከላከል ሥራውን የፖለቲካ አመራሩና የጤና ባለሙያዎች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
በመድረኩ የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ የዞን የወረዳ/የከተማ ጤና ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘገባው የሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።