የወባ ወረርሽኝ በቀጣዮቹ ወራት ልጠናከር ስለሚችል ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ልያደርግ እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ፥ ክልላዊ የወባ ወረርሽኝ መቆጣጠር ግብረኃይል በክልሉ እየተከናወነ ያለውን የወባ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ያለበትን ደረጃ በቦንጋ ከተማ ገምግሟል።
የወባ ወረርሽኝ የክልሉን ህዝብ hማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በመፍጠር እየተፈታተነ እንደሚገኝ የገለጹት የክልሉ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ ወረርሽኙ በማህበረሰቡ ላይ እያስከተለ ያለውን ዘርፈብዙ ጫና ለመቋቋም የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር አለበት ብለዋል።
በቢሮው እየተሰራ ያለው የወባ ወረርሽኝ የመከላከልና መቆጣጠር ስራው አበረታች ቢሆንም የሚመዘገበው ውጤት መዋዠቅ እያሳየ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የመከላከል ተግባሩን በባለቤትነት ስሜት በግብረ-ሃይል እየተገመገመ መምራት እንዳለበትም በአጽንኦት አስገንዝበዋል።
ከክረምት መዉጣት ጋር ተያይዞ የወባ ወረርሽኝ እስከ ህዳር አጋማሽ ባለው ጊዜ ሊጨምር ስለሚችል ህብረተሰብ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳሰቡት የክልሉ ጤና ቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ወረርሽኙን ለመግታት በየደረጃዉ ያለዉ አመራር፣ የጤና ባለሙያና የባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ወረርሽኙን ለመግታት ባለፋት ጊዜያት ግብረሀይል በማዋቀር በሰራው ስራ፤ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ያነሱት አቶ ኢብራሂም ይሁን እንጅ በተለያዩ ምክንያቶች መዘናጋት እየተፈጠረ በመሆኑ በአንዳንድ የክልሉ አከባቢዎች የወባ ወረርሽኙ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
በየመዋቅሩ የሚስተዋለው የመረጃ ጥራት ችግር ለወረርሽኝ መከላከል ስራው አንዱ ማነቆ እየሆነ መሆኑን የገለጹት አቶ ኢብራሂም ልዩ ትኩረት በሚሹ የክልሉ አካባቢዎች የፖለቲካ አመራሩ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
ወረርሽኙን ከመከላከል ረገድ ከማህበረሰብ አቀፍ የአከባቢ ቁጥጥርና የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች በተጓዳኝ የህክምናና መድኃኒት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ እየቀረበ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ኢብራሂም ቢሮው በመድሀኒት አቅርቦት፣ አስተዳደርና ቁጥርር ላይ ከሚመለከታቸው ኣካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመድረኩ የግብረሀይሉ ዝርዝር የአፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም አሁናዊ የክልሉ የወባ ወረርሽኝ ያለበት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።
የመድረኩ ተሳታፊ የባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ወረርሽኙ በህብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በዘመቻ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠይቀዋል።
ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በዋናነት ህብረተሰብን ያሳተፈ የአከባቢ ቁጥጥር ስራ እና አጎበር አጠቃቀም መጠናከር እንዳለበት ያሳሰቡት ተሳታፊዎቹ የህክምናና መድኃኒት አስተዳደር ተግባራት ተጠያቂነት ባለው መልክ መመራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የመከላከልና መቆጣጠር ተግባራት ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ ቁርጠኝነትና በተጠያቂነት መንፈስ መጠናከር እንዳለበት ያሳሰቡት የመድረኩ ተሳታፊዎች ቢሮው የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የከፋ የጤና ቀውስ እንዳይከሰት እያደረገ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ዘገባው የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።