የወባ ወረርሽኝ የህብረተሰቡ የጤና ስጋት በመሆኑ የመከላከል ሥራው ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለፀ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ቲም በሸካ ዞን ቴፒ ከተማና የኪ ወረዳ በወባ ወረርሽኝ መከላከል ላይ ያደረገውን የመስክ ምልከታ አስመልክቶ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቴፒ ከተማ ግብረ መልስ ሰጥቷል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ባለሙያ አቶ ተስፋ ፅዮን በውይይቱ እንደገለፁት ከዚህ በኃላ የምመጣው የወባ ስርጭት መጠን በጣም ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው መከላከል ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።
የሚደረጉ ድጋፎችን በሚመለከት ለወረርሽኙ መከላከል ተግባር በክልል ደረጃ ለመከላከል አቅም በፈቀደ መልኩ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልፀው የመድሀኒት ተደራሽነት ላይ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል ።
የክልሉ ምክር ቤት ህግ ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አምሳሉ ንጋቱ ባለፉት ወራት በቅንጅት በተሠራው ስራ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው የተጠናከረ ግምገማ በማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ወይዘሮ አምሳሉ አክለው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች በተደራጀ መንገድ ወቅታዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አካላት በሰጡት አስተያየት የወባ ወረርሽኝ አሁን ያለበት ደረጃ ከፍተኛ ስለሆነ አመራሩና ባለሙያዉ በቁርጠኝነት እስከ የታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን መስራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአካባቢ ቁጥጥር ሥራን መስራት የማፋሰስና የማዳፈን እና የአጎበር አጠቃቀም ላይ በሚገባ በመስራት የወረርሽኙን ደረጃ ለመቀነስ ከወትሮው በበለጠ በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
ከአጎበር አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የግንዛቤ እጥረቶችን መፍታት፤ወረርሽኙን ለመግታት እና ለመቆጣጠር በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠልና የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል ።
ቋሚና ጊዘያዊ የሆኑ መራብያ ቦታዎችን ማፋሰስና ማዳፈን ፤የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተተክሎ ከመስራት አንፃር ያሉ ክፍተቶችን መፍታት እንደሚገባም ተመላክቷል።
የጤና ጣቢያዎች የቦርድ ውይይት መቆራረጥ መኖር፤ በየወቅቱ ሪፖርት ያለመገምገም ፤በአንዳንድ ጤና ጣቢያ ላይ የመብራት መቆራረጥ ችግሮች መኖር ለቀጣይ መስተካከል እንደሚገባው ተነስቷል።
በቴፒ ከተማ ቴፒ ጤና ጣቢያ እና በየኪ ወረዳ ዝንክ ጤና ጣቢያና የኪ ጤና ኬላ በወባ ወረርሽኝ መከላከል ላይ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምልከታ ተደርጓል።
የዞን የወረዳ ከተማ አመራርና የጤና ማናጅመንት አባላት በግብረ መልስ መድረኩ ተገኝተዋል።
ዘገባው የሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው