የወባ ወረርሽኝ የመከላከል ዘመቻ በተቀናጀ ሁነታ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ ::

በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይረክተር ዶክተር እንዳለ ሳህሌ የተመራ ድጋፍና ክትትል ቡድን በሸካ ዞን የወባ ወረርሽኝ የመከላከል ዘመቻ ተግባራት ዙሪያ በቴፒ ከተማ ውይይት አድርጓል።
በውይይት መድረኩ የተገኙት የክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከል እና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር እንዳለ ሳህሌ የጤና ኤክስቴንሽን ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመው በየመዋቅሩ ኮማንድ ፖስት ማደራጀትና የጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎችን ትስስር በማጠናከር የወረርሽኙን ሥርጭት መቀነስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሴቶች ልማት ህብረት በሌለበት በጤና ኤክስቴንሽን ስራዎች ውጤታማ መሆን እንደማይቻል ገልፀው የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀቶችን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።
የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ካይቶ በበኩላቸው የታካሚ መረጃን በተደራጀ መንገድ ከመያዝና ሪፖርት ከማድረግ አንፃር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመፍታት መረጃዎችን በመተንተን በአግባቡ መያዝ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ህገ ወጥ የመድኃኒት ቁጥጥርና ክትትል በአንድ ወገን የሚቻል ባለመሆኑ ሁሉም በተቀናጀ መንገድ በመከላከል አንድም እናት በመድኃኒት እጦት እንዳትሞት መስራት ይገባናል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየትና ጥያቄ ያነሱ ሲሆን የጤና ልማት ሠራዊት የሴቶች ልማት ህብረትን ማጠናከር የመረጃ ልውውጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን መሙላት የተጀመረው የወባ ወረርሽኝ መከላከል ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሚከናወኑ ተግባራትን ቆጥሮ የሪፖርት አካል ያለማድረግና የመረጃ ልውውጥ ላይ ክፍተቶች መኖር የግብዓት እጥረት መኖሩ ከውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሱ ተግዳሮቶች ናቸው።
ከህክምናው ይልቅ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ ላይ ትኩረት መስጠት ሌሎች የጤና ተግባራትን ከወባ መከላከል ጋር በተቀናጀ መንገድ ማከናወን የጤና መደበኛ ስራዎችን በማጠናከር የተጀመረውን የወባ መከላከል ዘመቻውን አጠናክሮ መሄድ ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በመድረኩ የወባ ወረርሽኝ የመከላከል ዘመቻ አፈፃፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ በስፋት ውይይት ተደርጎ መድረኩ ተጠናቋል።
ዘገባው የሸካ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።