የዜጎችን የመክፈል አቅም ታሳቢ ያደረገ የማዐጤመ ክፍያ ተግባራዊ ልደረግ ነው
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ የዜጎችን የመክፈል አቅም ታሳቢ ያደረገ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና አገልግሎት መዋጮ ማስፈጸሚያ ሰነድ ላይ ከማዐጤመ ቦርድ አባላትና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በቦንጋ ከተማ መክሯል።
በብሄራዊ ምክር ቤት የቀረበውን የመዋጮ መመሪያ በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች ተግባራዊ በማድረግ የጤና አግልግሎት ፍትሀዊ ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የጠቆሙት የክልሉ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ በጤና ተቋማት በአግልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየው ማነቆ መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአባል ማፍራት ተግባር በክልሉ ሁሉም አከባቢ በመዋቅር ደረጃ ውጤታማ በሆነ መልኩ መተግበሩ አበረታች መሆኑን የገለጹት አቶ ነጋ ነገርግን በግለሰብ ደረጃ የአባል ማፍራት ተግባሩ ልዩ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት።
ተሻሻሎ የቀረበውን የገቢ አቅምን መሠረት ያደረገ የአባልነት መዋጮ በየደረጃው ልየታ በማድረግ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ያስገነዘቡት አቶ ነጋ የዕድሳት እንዲሁም አዲስ አባል የማፍራት ተግባር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የተሻለ እንዲሆን የፖለቲካ አመራሩ ተግባሩን በቁርጠኝነት መምራት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የዜጎችን የጤና ሁኔታ ማሻሻል የብልጽግና ፓርቲ ቁልፍ የማህበራዊ ብልጽግና ግብ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ጤና መድህን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በክልሉ በጤና መድህን የተገኘውን አመርቂ ውጤት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለው በክልሉ ፍትሀዊ የጤና አግልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተጀመረው የማዐጤመ ተግባር እንዲሳካ የአመራር ቁርጠኝነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
የጤና መድህን ተግባር በጤና ሴክተር የማይገደብ በመሆኑ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ትብብር መጠናከር እንዳለበት የጠየቁት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በተላይ ለዚህ ተግባር የሚሰበሰበውን የህዝብ ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባ ተናግረዋል።
አቶ ኢብራሂም አክለው በቀደመው ውጥ በሆነው የመዋጮ ስረዓት የፍትሃዊ ጤና ተደራሽነት በዘላቂነት ማረጋገጥ አዳጋች በመሆኑ የገቢ አቅምን መሠረት ያደረገ መዋጮ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ተግባሩ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ ኃላፊነቱን በጋራ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ ከአባላት መዋጮ መሰብሰቡን የገለጹት በክልሉ ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምትኩ ታመነ ከዚህም ውስጥ 44 ሚሊዮን ብር ለህክምና አግልግሎት ወጪ ተደርጎ መከፈሉን ተናግረዋል።
በክልሉ በ56 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች ከ292 ሺህ በላይ አባላትን ማፍራት መቻሉን የገለጹት አቶ ታመነ በቀጣይ የነባር አባላት እድሳትና የአዲስ አባል ማፍራት ስራ ትኩረት ተሰጥተው እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
የተሻሻለው የማዐጤመ መዋጮ ማኑዋል በዝርዝር ቀርቦ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል።
ተግባሩን በተሻለ ደረጃ ለመፈጸም የተጀመረው ድጋፋዊ ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት የመድረኩ ተሳታፊዎች የመዋጮ ማስፈፀሚያውን በየደረጃው ውይይት በማድረግ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የሚሰበሰበውን ገንዘብ በወቅቱ ወደ አንድ የዞን የሀብት ቋት ማስገባት እንደሚገባ የገለጹት ተሳታፊዎቹ የድሀ ድሀ የትናጥል ድጎማ ገንዘብ በጊዜ በየደረጃው ያለው መዋቅር በቁርጣኝነት ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ዘገባው የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው።