የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ በአቶ ኢብራሂም ተማም የተመራው ልዑክ ቡዱን በወረዳው በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖቻቸው የተለየዩ የህክምና መድኃኒቶችን ድጋፍ አበርክቶላቸዋል ።
በዳውሮ ዞን ማሪ ማንሳ ወረዳ በናዳ እና መሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የህክምና መድኃኒቶች እና ግብዓቶችን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ድጋፍ አድርጓል ።
አቶ ኢብራሂም ተማም የህክምና ግብዓት ድጋፍ ለወረዳው መንግሥት ሲያስረክቡ እንደተናገሩት በናዳ ምክኒያት ለተጎዱት ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ የሚቀጥል እንደሆነና ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚደረግ ሀሳባቸውን ገልጸዋል ።
በተጨማሪም የጤና ቢሮ ልዑክ በማሪ ጤና ጣቢያ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ እና አጠቃላይ የተቋሙን ውስጣዊ ገጽታ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የተስተዋሉ ጉድለቶችን የማረም እና ጥንካሬዎች የማስቀጠል ሀላፊነት በመስጠት በዚህ ወቅት የህዝብ ጤና እያወከ ያለውን የወባ በሽታ መከላከል እና ህክምና ስራ በልዩ ቅኝት የወረዳው መንግሥት እና የጤና መዋቅሩ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል ።
ድጋፉን የተረከቡት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ተካልኝ በቀሌ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊነቱን ለመወጣት እና የህዝቡን ችግር ለመጋራት ያሳየውን ወገንተኝነት በማድነቅ ምስጋና አቅርበዋል ።
አያይዘውም በማሪ ጤና ጣቢያ ውስጥ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የተመለከቱት የጤና ተቋሙ ስራ እጅግ ወሳኝ የሆኑ ግብዓት እጥረት ላይ የክልሉ ጤና ቢሮ ድጋፍ እንዲያደርግ አመላክቷል ።
በተመሳሳይም በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ እና በቤንች ሸኮ ዞን ሰሜን ቤንች ወረዳ በመሬት መንሸራተት ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የሚውል የመድሀኒት እና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የቢሮው ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ገልፀዋል።