የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጂማ ቅርንጫፍ ጋር በመቀናጀት በቤንች ሸኮና ሸካ ዞኖች ግማሽ ሚሊየን ብር የሚጠጋ የተበላሹና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግብና መጠጦችን ማስወገዱን አስታወቀ።
ህብረተሰቡ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ባዕድ ነገር የተቀየጡ ምግቦችን ሲመለከት በአቅራቢያቸው ለሚገኝ የጸጥታ አካላትና በ8284 በነጻ በመደወል ጥቆማ መስጠት እንዲተባበሩ ጥሪ ቀርቧል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጂማ ቅርንጫፍ ጋር በመቀናጀት በቤንች ሸኮ እና ሸካ ዞን በምግብና መጠጥ አከፋፋዮችና የችርቻሮ ሱቆች የክትትልና የቁጥጥር ስራ መስራቱን ገልጿል።
በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ጉዳዮች ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱልአዚዝ ፈረጃ እንደተናገሩት እንደ ክልል በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማንና በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ላይ በምግብና መጠጦች ላይ የቁጥጥር ስራ ተሰርቷል ብለዋል። ተግባሩ ከምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጂማ ቅርንጫፍ ፣ ከየዞን ጤና መምሪያዎችና ከንግድ ዘርፍ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በሰራቱን ገልጸዋል።
በቁጥጥር ስራው ግምታዊ ዋጋቸው ከ450ሺ በላይ የሆኑ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው የታሸጉ ጁሶች ፣ ጨው ፣ የንግድ ምልክት የሌላቸው የአልኮል መጠጦች እና በተለይም አፍላ ቶክሲን ሊያስከትሉ የሚችሉ የሻገቱ በርበሬዎች በስፋት መገኘታቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ግብዓቶች በህብረተሰቡ ጤና ሊያስከትሉ የሚችሉት ጉዳት ከባድ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብዱልአዚዝ የክልሉ ጤና ቢሮም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም እንደ ማር ፣ ቅቤና በመሳሰሉ ምግቦች ላይ ባዕድ ነገሮችን ቀይጠው የሚያቀርቡ አካላት ላይ ከአስተዳደራዊ እርምጃ ባሻገር በህግ የማስጠየቅ ስራም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ጂማ ቅርንጫፍ የምግብ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዮናስ ሞላ እንደተናገሩት በቤንች ሸኮ ሚዛን አማንና በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ከ168 ተቋማት በላይ የቁጥጥር ስራ መሰራቱን አቶ ዮናስ ጠቁመዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቤንች ሸኮና ሸካ ዞን በተደረገ ፍተሻ ግምታዊ ዋጋቸው ከ450ሺ ብር በላይ የሆኑ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ ፣ በአቀማመጥ ምክንያት የተበላሹ ምግብና መጠጦች ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በቤንች ሸኮ ዞን ጤና መምሪያ የጤናና ጤና ነክ ግብዓት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት የቡድን መሪ አቶ ለገሰ ግርማዬ እንደተናገሩት ከቅርንጫፍ መስረመያ ቤትና ከክልሉ ጤና ቢሮ የቁጥጥር ቡድን ጋር ለባለፉት 3 ቀናት በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር 118 ተቋማት ላይ የቁጥጥር ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በዚህም ግምታዊ ዋጋቸው ሩብ ሚሊየን የሚጠጋ የተበላሹ የፋብሪካ ውጤቶችና የአካባቢ ምግቦችን ከገበያ የማስወጣት ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። ለስራው ስኬት የህብረተሰቡ ጥቆማና ትብብር ከፍተኛ ነበር ያሉት አቶ ለገሰ ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ዘገባው የቤንች ሼኮ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ነው